በኦሮሚያ ክልል በአዲሱ ዓመት የወተት ምርታማነት ለማሳደግ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ላሞችን ዝርያ የማሻሻል ስራ ይከናወናል- ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በአዲሱ ዓመት የወተት ምርታማነት ለማሳደግ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ላሞችን ዝርያ የማሻሻል ስራ ይከናወናል- ቢሮው
ቦቆጂ ፤ ነሐሴ 29/ 2015(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በአዲሱ የበጀት ዓመት የወተት ምርታማነት ለማሳደግ በሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የወተት ላሞችን ዝርያ የማሻሻል ስራ እንደሚከናወን የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ አስታወቁ።
በክልሉ ደረጃ በተሻሻለ የኮርማ ዝሪያ በሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ ዝርያ የማሻሻል ስራ በአርሲ ዞን ሌሙና ቢልብሎ ወረዳ ሌሙ ቀበሌ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የግብርና ቢሮው ሃላፊ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የአርሲ ዞን ከሰብል ልማት ባሻገር በእንስሳት ሀብት የሚታወቅ ነው።
ዛሬ በዞኑ የተጀመረው ዘመናዊ ሰው ሰራሽ የወተት ላሞችን ዝርያ የማሻሻል ስራ ወደ ሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች በማስፋፋት የወተት ምንጭ ለማድረግ ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።
የአርሲ ዞን አርሶ አደሮች በሰው ሰራሽ ዝርያ የማሻሻል ስራ ቀድመው በመጀመር ውጤቱን እያጣጣመና የእንስሳት ኢንሼቲቪ በተግባር እውን እየሆነ ማሳያ ነው ብለዋል።
እንደ ክልል በአዲሱ የበጀት ዓመት የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ላሞችን በሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ ዝርያ የማሻሻል ስራ ይከናወናል ብለዋል።
በክልሉ ከ25 ሚሊዮን በላይ የወተት ላሞች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ጌቱ፤ በሰው ሰራሽ ዝርያ ለማሻሻል ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ በዘመናዊ የአሰራር ዘዴዎች የማምረት ስራ ከግብርና ሚኒስቴርና የምርምር ተቋማት ጋር እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል ።
የኢትዮጵያ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ በበኩላቸው፤ የአርሲ ዞን ከስንዴና ገብስ ልማት ሌላ የኢትዮጵያ የወተት ምንጭ ለማድረግ የመጀመሪያው ምዕራፍ መጀመሩን ገልጸዋል።
በተለይ በሰው ሰራሽ ዝርያ የማሻሻል ስራ በርካታ የወተት ላሞችን በአንድ ጊዜ ማዳቀል እንደሚቻል አመልክተዋል።
ሀገራችን ከ25 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በየዓመቱ እያወጣች ወተትና የወተት ተዋጽኦ ከውጭ እያስገባች ነው ያሉት ዶክተር አስራት ፤ በአርሲ ዞን ዛሬ የተጀመረውና ተስፋፍቶ የሚቀጥለው የሰው ሰራሽ ዝርያ የማሻሻል ስራ የወተትና ወተት ተዋጽኦን በሀገር ውስጥ ለመተካት መሰረት የሚጥል መሆኑን አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በክልሉ የተጀመረውን የወተት ላሞችና ዘመናዊ የእንስሳት ኢንሼቲቭ የኮሮማ ዝሪያዎችን በማቅረብ ጭምር ዕገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የአርሲ ዞን አስተዳደር አቶ ኢብራሂም ከድር ፤ ዞኑ በእንስሳት ሀብት የሚታወቅ በመሆኑ የልማት ትሩፋት ፕሮግራም ለማሳካት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ከአስራ ሁለት ሚሊዮን በላይ የእንስሳት ሀብት በዞኑ መኖሩን ጠቅሰው፤ ከመካከላቸውም 618ሺህ የወተት ላሞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአርሲ ዞን 26 ወረዳዎች 127ሺህ እንስሳትን ዝርያ ለማሻሻል ታቅዶ ስራው ዛሬ መጀመሩንም ጠቅሰዋል።
በተጓዳኝም የእንስሳት ክትባት እንዳለም ጠቁመዋል።
የሌሙና ብልብሎ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሂርጳ ተሾመ በበኩላቸው፤ በወረዳው በዓመት 17ሚሊዮን 445ሺህ ሊትር ወተት ይመረታል ብለዋል።
በአማካይ በቀን እስከ 42 ሊትር ወተት የሚሰጡ የተለያዩ ዝሪያ ያላቸው ከ200ሺህ በላይ የወተት ላሞች መኖራቸውንም አመልክተዋል።