የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የልማት ስኬትና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሁላችንም የጋራ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የልማት ስኬትና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሁላችንም የጋራ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 29/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የልማት ስኬትና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሁላችንም የጋራ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ስለ-ኢትዮጵያ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ የሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የልማት ስኬት፣ እድገትና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሁላችንም የጋራ ጉዳይ ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ሁላችንም በጋራ ከቆምን የማናሳካው የልማት እቅድ የማንሻገረው ችግር አይኖርም ያሉት ከንቲባዋ፤ ኢትዮጵያውያን በጋራ ጉዳያችን በመመካከር፣ በመነጋገርና በመከራከር አገራችንን መገንባት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌትነት ታደሰ፤ በበኩላቸው የጋራ እሴቶች ላይ እየመከርን አብሮነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን ማስቀጠል የሁላችንም ሀላፊነት መሆን አለበት ብለዋል።
በተለያዩ መድረኮች ስለ ኢትዮጵያ የተካሄዱ መድረኮች ለችገሮች የጋራ መፈትሄ በመፈለግ፤ ስኬቶችን በጋራ ማስቀጠል ዓላማ አድርገው መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
በ13 የተለያዩ ከተሞች ስለ ኢትዮጵያ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን አንስተው በዛሬው እለት የ14ኛው መድረክ ማስጀመሪያ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ቀደም ሲል የተካሄዱት መድረኮች ተጨባጭ ውጤቶች የተገኙባቸው ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል።
በዛሬው መድረክ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራንና ሌሎችም ታድመዋል።