ቀጥታ፡

በዚህ የበጀት ዓመት አምስት የሚጠጉ የኳራንታይን ጣቢያዎች ተለይተው የሚያስፈልጋቸውን የማሸነሪና መሳሪያ ማሟላት በስትሪንግ ኮሚቴ ፈቅደናል- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2015(ኢዜአ)፦በዚህ የበጀት ዓመት አምስት የሚጠጉ የኳራንታይን ጣቢያዎች ተለይተው የሚያስፈልጋቸውን በማሸነሪና መሳሪያ ማሟላት በስትሪንግ ኮሚቴ ፈቅደናል ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ ተናገሩ።

የኳራንቲን ጣቢያዎች የቁም እንስሳት ጥራት ከበሽታ ነፃ የሆኑ፣ የተቀባይ አገራትን ደረጃ ያሟሉና በትክክለኛ መስፈርት ለገበያ ለማቅረብ ወሳኝ ናቸው።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ለማሳለጥ የሚሌ የኳራንቲን ጣቢያ በቅርቡ ስራ መጀመሩ ይታወቃል።

ከሚሌ በተጨማሪ በዚህ የበጀት ዓመት አምስት የሚጠጉ የኳራንታይን ጣቢያዎች ተለይተው የማሸነሪና መሳሪያ ማሟላት ስራ የሚከናወን መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ ተናግረዋል።

የቁም እንስሳትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ መንግስት ሰፋፊ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም የሚሌ ኳረንቲን ጣቢያ የኢትዮጵያ ኦሪጂን ኦፍ ሰርተፊኬት ያላቸውን የቁም እንስሳት ወደ ውጪ አገራት መላክ ጀምሯል ነው ያሉት።

የቁም እንስሳት ቀደም ሲል በጅቡቲ ኳራንቲን ወደ ውጭ አገራት ይላክ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሌ ኳራንቲን ከ7 ሺህ በላይ በጎችን ወደ ሳዑዲ አረቢያ መላክ ተችሏል ብለዋል።

የሚሌ ኳራንቲን ወደ ስራ መግባቱ በቁም እንስሳት ሃብት የሚስተዋለውን ኮንትሮባንድ በማስቀረት ረገድ የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት ልማት የውጪ ምንዛሪ በማግኘት በዘርፉ ተጠቃሚነቷ እንዲያድግ ለማስቻል ከሚሌ በተጨማሪ በዚህ የበጀት ዓመት አምስት የሚጠጉ የኳራንታይን ጣቢያዎች ተለይተው የሚያስፈልጋቸው የማሸነሪና መሳሪያ ማሟላት በስትሪንግ ኮሚቴ ፈቅደናል ብለዋል።

ከሳዑዲ በተጨማሪ ወደ ግብጽ፣ ኦማን፣ ጅቡቲ እና የመን ከሚሌ ኳራንቲን የቁም እንስሳትን ለመላክ ከአገራቱ ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም