ከልዩነት አጥር በመውጣት በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት አለብን- ሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ከልዩነት አጥር በመውጣት በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት አለብን- ሰላም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 28/2015 (ኢዜአ)፡- ከልዩነት አጥር በመውጣት በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ተናገሩ።
“አገራዊ ማንነት ለጠንካራ አገር ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር አላማ ያደረገ የፓናል ውይይት በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የሰላም ሚኒስቴር ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።
በመድረኩ ላይ በመገኘት መልእከት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፤ ለዜጎች ነጻነት፣ ሰላም፣ ክብርና ጥቅም መከበር ሀገር መሰረት ስለመሆኗ ጠቅሰዋል።
በዜጎችና በልሂቃን መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴታው፤ ከልዩነት አጥር በመውጣት በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት አለብን ብለዋል።
የጋራ ማንነቱን ጠንቅቆ ያልተረዳ ሕዝብ ስለ ትናንት ታሪኮቹ፣ ስለ ጋራ ጥቅሞቹ፣ ስለ መልካም እሴቶቹና ስለ ነገ ዓላማዎቹ ማወቅ ያዳግተዋልም ነው ያሉት።
በመሆኑም ዜጎች የጥቅማቸው፣ የክብራቸውና የነጻነታቸው ዋስትና የሆነች ጠንካራ ሀገር በጋራ ለመገንባት መስራት አለባቸው ብለዋል።
የጠንካራ የአገር ግንባታ መሰረቱ የሕዝብ አንድነት በመሆኑ ሁላችንም ለሀገራችን ልማትና እድገት መጋራ መቆም አለበን ነው ያሉት።
በመድረኩ የተለያዩ ይዘቶችን የያዙ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።