ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ የዜጎችን አብሮነት በማጠናከር የኢትዮጵያን ከፍታ እውን የማድረግና በሰጥቶ መቀበል መርህ የፖለቲካ ባህልን በማጎልበት መልካም እድል የፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

አዲሰ አበባ፤ ነሐሴ 28/2015 (ኢዜአ)፡- የመደመር እሳቤ የዜጎችን አብሮነት በማጠናከር የኢትዮጵያን ከፍታ እውን የማድረግና በሰጥቶ መቀበል መርህ የፖለቲካ ባህልን በማጎልበት መልካም እድል የፈጠረ መሆኑ ተገለጸ።

''መደመር የዘመኑ አርበኝነት" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በጅግጅጋ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የታደሙት የሕግ ምሁሩ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዛዲግ አብርሃ፣ በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ፣ የሱማሌ የአገር ሽማግሌዎች ሸንጎ እና የሰላምና አንድነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ የመወያያ ጽሁፎችን አቅርበዋል።

"መደመር የኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ሮባ፤ የኢትዮጵያን ከፍታ እውን ሊያደርጉ የሚችሉ አስተሳሰቦችና ሀብቶች በሁሉም አካባቢዎች ስለመኖራቸው ጠቅሰዋል።

መደመር ለኢትዮጵያ ከፍታ መንገድ መጥረጉን ገልጸው፤ የፍረጃ አካሄድን ወደ ጎን በመተው ለሕብረ- ብሔራዊ አንድነት ትኩረት በመስጠት የጋራ ቤታችን የሆነችው ሀገራችንን ከፍታ ማረጋገጥ ይገባናል ብለዋል።

በመሆኑም የመደመር እሳቤ የዜጎችን አብሮነት በማጠናከር የኢትዮጵያን ከፍታ እውን የማድረግና በሰጥቶ መቀበል መርህ የፖለቲካ ባህልን በማጎልበት መልካም እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ የመደመር እሳቤ አገር በቀል እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሐቅና እሴቶች ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በትብብር መሥራትን የሚያበረታታ የአርበኝነት መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተደመረ አቅም ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር በጋራ ጥረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ፤ ''በመደመር ሰጥቶ መቀበል'' በሚል ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ በመደመር ማዕቀፍ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሶማሌ ክልልና ሕዝብ ብዙ ማትረፋቸውንም ገልፀዋል። 

በክልሉም ሆነ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመነጋገርና በመተባበር መፍታት መቻሉንም ጠቅሰዋል። 

የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ጠንካራ ትስስር ፈጥረው የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው በመሥራት ላይ ናቸው ብለዋል።
 

የመደመር እሳቤ ለአገር በቀል የእርቅ ሽምግልና ሥርዓቶች እውቅና የሰጠ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሶማሌ የአገር ሽማግሌዎች ሸንጎ እና የሰላምና አንድነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ ናቸው።

ኢትዮጵያ የበርካታ የአገር በቀል የሽምግልና ሥርዓቶች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፤  የመደመር እሳቤ ለአገር በቀል እውቀቶች እውቅና በመስጠቱ ሊደነቅ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ በሶማሌ ክልል የአገር ሽማግሌዎች አደረጃጀት በመፍጠር ጭምር በልማትና ዘላቂ ሰላም ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን በመከላከል ሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በጋራ እንስራ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎችም ጥያቄና አስተያየት ተነስቶ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም