የመደመር እሳቤ ሀገርን በጋራ ጥረት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል የዘመኑ አርበኝነት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ ሀገርን በጋራ ጥረት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል የዘመኑ አርበኝነት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ
አዲሰ አበባ፤ ነሐሴ 28/2015 (ኢዜአ)፡- የመደመር እሳቤ ሀገርን በጋራ ጥረት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል የዘመኑ አርበኝነት መሆኑን የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጋር በመተባበር ''መደመር የዘመኑ አርበኝነት'' በሚል መሪ ኃሳብ በጅግጅጋ ከተማ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩም የሶማሌ ክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች ተሳታፈዋል።
በመድረኩ የመደመር እሳቤን መሰረት ያደረጉ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመድረኩ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድን መልዕክት ያቀረቡት በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌ፤ የመደመር እሳቤ አገርን እንዴት በትብብር ማሳደግ እንደሚቻል አዲስ መንገድ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢዜአ የመደመር እሳቤን መሰረት ያደረጉ የፓናል ውይይት በማዘጋጀት ዜጎች በሀሳቡ ላይ እንዲወያዩ እያከናወነ ያለውን ሥራም አድንቀዋል።
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሶማሌ ክልል የተገኙ ድሎችን እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ አዜአ እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን ከውጭ ከሚመጣ የፖለቲካ ርዕዮት ጥገኝነት ያላቀቀ የእኛ የኢትዮጵያውያን መንገድ ነው ብለዋል።
ያለንበት ዘመን አርበኝነት በመደመርና በመሰናሰል ሀገራዊ ብልፅግናን በጋራ ጥረት የማረጋገጥ ተልዕኮን ማሳካት መሆኑንም በአፅንኦት ተናግረዋል።
የመደመር እሳቤ ለመረዳዳትና ለማደግ ማዋል እንደሚገባ አሳይቶናል ነው ያሉት።
ከዚህ አኳያ ልዩነቶችን በግጭት እንዲሁም ፍላጎትን በኃይል ለመጫን መሞከር አፍራሽ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ አፍራሽ አካሄድ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለከፋ ችግር እንደሚዳርግ ጠቅሰው፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት አገርን በትብብር ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሻገር ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን የሥራ ባህል በመለወጥና የእይታን አድማስ በማስፋት ትውልዱ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እንዲያረጋግጥ ጉልህ አስተዋጽኦ በማበረከት ላይ ይገኛል ብለዋል።
የመደመር እሳቤን እርስ በእርስ ባለን መስተጋብር ለአገርና ለህዝብ እንዲሁም ለቆዩ ችግሮች የመፍትሄ አማራጭ በማቅረብ በኩል የተለያዩ መጽሐፍቶች ተጽፈውበት ለህዝብ ተደራሽ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በመደመር እሳቤዎች ዙሪያ የአገራችን ህዝቦች ግንኙነት ጠንካራ እንዲሆንና ኢትዮጵያን የብልጽግና ማማ ላይ ለማድረስ እንዲቻል የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ላይ ስለመሆኑም ተናግረዋል።