ቀጥታ፡

የማረሚያ ቤቶች ሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ሥርዓት ወጥ ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ ነው - ኮሚሽነር ጀነራል ዳመነ ዳሮታ

ሚዛን አማን ነሐሴ 28/2015 (ኢዜአ)...የማረሚያ ቤቶች ሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ሥርዓት ወጥ ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዳመነ ዳሮታ አስታወቁ።

16ኛው የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።

ኮሚሽነሮቹ ከጉባኤው ጎን ለጎን አዲሱን የሚዛን ማረሚያ ተቋም ጎብኝቷል።

ኮሚሽነር ጀነራል ዳመነ ዳሮታ በወቅቱ ለኢዜአ እንዳሉት ማረሚያ ተቋማት የታራሚዎችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ የማረምና የማነጽ ሥራ መፈጸም አለባቸው።

"በማረሚያ ቤቶች ጥበትና በሌሎች አገልግሎቶች እጥረት እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ እየተሰራ ነው "ብለዋል።

ለአብነትም የማረሚያ ቤት ጥበት ችግር ለመፍታት የማስፋፊያ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል ።

የሚዛን ማረሚያና ወደ ሥራ የገባውን የቦንጋ ማረሚያ ተቋም በማሳያነት አንስተዋል።

በዚህም የማረሚያ ቤቶች ሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ሥርዓት ወጥ ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑን  ኮሚሽነር ጀነራል ዳመነ ዳሮታ አስታውቀዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳዊት ጢሞቴዎስ በበኩላቸው "ታራሚዎች ሕጉ የፈቀደላቸውን መብቶች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማስቻል ያስፈልጋል" ብለዋል።

የታራሚዎች እለታዊ የምግብ ፍጆታ ተመን ከብዙ አመታት በፊት የተሰራ በመሆኑ ከወቅቱ ጋር አስተሳስሮ ለማስተካከል ኮሚሽኑ ጥናት በማድረግ ላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

"ከመኝታ ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በማድረግ ታራሚዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲታረሙ ከአጋር አካላት ጋር ተባብረን እንሰራለን" ሲሉም አክለዋል።

 "ከዚህ ቀደም የነበረው ማረሚያ ተቋም በጭቃ የተሰራና ጠባብ ከመሆኑ ባሻገር ከተማ ውስጥ በመሆኑ ፍሳሽ ለማስወገድና የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት ጠብቆ ለማረም እንቸገር ነበር " ያሉት ደግሞ የሚዛን ማረሚያ ተቋም ሀላፊ ኢንስፔክተር ጌትነት ፍቃዱ ናቸው ።


 

አሁን ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ በተሰራው ተቋም በአግባቡ የማረምና ማነጽ ሥራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል ።

የውሀ እጥረት ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል ።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም