በቴል አቪቭ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ከፖሊስ ጋር በፈጠሩት ግጭት 160 ሰዎች መቁሰላቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ) ፦ በእስራኤል ቴል አቪቭ የሚኖሩ ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራዊያን ከፖሊስ ጋር በፈጠሩት ግጭት ፖሊሶችን ጨምሮ 160 ሰዎች መቁሰላቸው ተገለጸ።

እንደ እየሩሳሌም ፖስት ዘገባ የኤርትራ ኤምባሲ በቴል አቪቭ ያቀረበውን የባህል ዝግጅት ኤርትራዊያኑ ስደተኞች በመቃወማቸው ምክንያት በተነሳ ብጥብጥ ብዙዎቹ ጉዳት ደርሶባቸዋል።


 

በተቃውሞው ላይ በነበራቸው ተሳትፎ ከቆሰሉት ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራዊያን መካከል ስምንቱ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው።

እየሩሳሌም ፖስት የሆስፒታልና የፖሊስ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከቆሰሉት መካከል 13ቱ መጠነኛ እንዲሁም 93 የሚሆኑት ደግሞ ቀላል ጉዳት ያጋጠማቸው ናቸው።


 

ዛሬ ከቀትር በኋላ በቴል አቪቭ የኤርትራ ኤምባሲ ባሰናዳው ዝግጅት ላይ በተነሳው የተቃውሞ ብጥብጥ 50 የሚሆኑ ፖሊሶች መቁሰላቸውን ጨምሮ በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል።

ኤርትራዊያኑ ስደተኞች የሃገራቸውን መንግስት በመቃወም በተነሳው ብጥብጥ የሱቆችን መስኮቶች፣ የፖሊስ ተሽርካሪዎችን የሰባበሩ ሲሆን ፖሊስም ሁኔታውን ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስና ሌሎችንም አማራጮች መጠቀሙ ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም