ቀጥታ፡

ከቡና የሚገኘውን  የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ የድርሻየን እየተወጣሁ ነው  - ማእከሉ

ሐዋሳ ፣ነሃሴ 27/2015 (ኢዜአ) ሀገሪቱ  የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን  በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የሀዋሳ ምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማእከል አስታወቀ።

ማእከሉ በተያዘው 2016 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ለሚቀርብ 77ሺ ቶን ቡና  የጥራት ደረጃ ለመስጠት አቅዶ እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

ማእከሉ የ2015 በጀት አመት አፈጻጻም የገመገመበትና በ2016 እቅድ ላይ የመከረበት የአንድ ቀን መድረክ ዛሬ በሻሸመኔ ከተማ ተካሂዷል ።

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የሃዋሳ ምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማእከል አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ሲማ እንዳሉት  ማእከሉ ሚያዚያ 3 ቀን 2015 ዓም ስራውን በይፋ ጀምሯል።

"የማእከሉ መከፈት ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለአለም ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ ቡና የአካባቢውን ጣዕም ይዞ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ የሚያስችል ነው" ብለዋል።

ማእከሉ ስራ ከጀመረ በኋላ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ ከ21 ሺህ 900 ቶን በላይ ቡና መርምሮ የጥራት ደረጃ መስጠቱንና ለውጭ ገበያ  ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ መላኩን ገልጸዋል።

ከተላከው ቡና ከ9 ሺህ 700 ቶን በላይ የሚሆነው የታጠበና ቀሪው ያልታጠበ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው የጥራት ደረጃ ከወጣለት ቡና 74 ከመቶው ደረጃ አንድና ሁለት መሆኑንም ተናግረዋል ።

"የምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማእከሉ ወደ አምራቹ መቅረቡ የቡና ጥራት ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው" ብለዋል።

የማእከሉን አቅም በማሳደግ ወደአምራቹና ኢንደስትሪዎች ቀርቦ በመስራት የጥራት ደረጃውን ለመጨመር በቅንጅት መስራት ተገቢ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በማእከሉ ከሲዳማ ጨምሮ ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ለሚገቡ ቡናዎች የጥራት ደረጃ የሚሰጥ ቢሆንም የቢሮ እጥረትና የመሰረተ ልማቶች አለመሟላት የመሳሰሉ ተግዳሮቶች ያሉበት በመሆኑ ለመፍትሄው እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ።

ማእከሉ በተያዘው  2016 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ለሚቀርብ ከ77 ሺህ ቶን በላይ ቡና የጥራት ደረጃ ለመስጠት አቅዶ እየሰራ መሆኑን  የገለጹት ደግሞ የማእከሉ ዴስክ ሃላፊ አቶ የትናየት ሸዋ ናቸው። 


 

በማእከሉ የሚሰጠውን የምርት ጥራት ደረጃ በተገቢው በማከናወን ጥራቱን የጠበቀ ቡና በማቅረብ እንደ ሀገር ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የማእከሉ ናሙና አውጭ አቶ ብርሃኑ አስታጥቄ በማእከሉ የሚያከናውነው አገልግሎት ኢትዮጵያ በአለም ገበያ እንድትወዳደር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም ጥራት ያለው ቡና ለአለም ገበያ እንዲቀርብ በማድረግ ሙያዊ ግዴታውን እንደሚወጣ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ብቻ ይሰጥ የነበረውን የምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ስራ ለማስፋፋት ባለፈው ዓመት ከከፈታቸው ማእከላት የሀዋሳው የምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማእከል አንዱ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም