በጎንደር ከተማ በህዝቡና በፀጥታ ሃይሉ የነቃ ተሳትፎ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በመመለሱ የሰዓት እላፊ ገደብ መሻሻሉን ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ በህዝቡና በፀጥታ ሃይሉ የነቃ ተሳትፎ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በመመለሱ የሰዓት እላፊ ገደብ መሻሻሉን ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ
ጎንደር ፤ ነሐሴ 27/2015(ኢዜአ)፡-በጎንደር ከተማ በህዝቡና በፀጥታ ሃይሉ የነቃ ተሳትፎ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በመመለሱ ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ መሻሻሉን የኮማንድ ፖስቱ አባልና የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ አስታወቁ፡፡
ረዳት ኮሚሽነሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ በከተማው ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል።
የከተማው ነዋሪ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆኖ ባደረገው እንቅስቃሴ ሰላም ማስፈን መቻሉንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በከተማው የሰውና የተሸከርካሪ እንዲሁም የግልና የመንግስት ተቋማት እንቅስቃሴ በተሟላ ሁኔታ ወደ መደበኛ ስራቸው መግባታቸውን ተናግረዋል።
የተገኘውን ሰላም የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠል የከተማውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንዲቻል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጥሎ የነበረውን የሰዓት ገደብ እንዲሻሻል መደረጉን አስታወቀዋል።
እንዲሁም መጪው የዘመን መለወጫ በዓል ከመሆኑ አንጻር የሰዓት ገደቡ ማሻሻል ወሳኝ ሆኖ መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
በተደረገው ማሻሻያም በከተማው ተጥሎ የነበረው የሰውና የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ ምሽት አንድ ሰዓት የነበረው ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ወደ ሁለት ሰዓት እንዲራዘም ኮማንድ ፖስት መወሰኑን ገልጸዋል።
የከተማው ህዝብ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነት ቀና ትብብር ከማድረጉም በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የከተማው ሰላምና ጸጥታ እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውቀዋል።
ህዝቡ በህግ ማስከበር ስራው ያበረከተውን አስተዋጽኦ በማጠናከር የተገኘው ሰላም ይበልጥ አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመቆም የጀመረውን እገዛ እንዲቀጥልም ረዳት ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በከተማው የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቀጣይ ደረጃ በደረጃ እንደሚነሳም ረዳት ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡
All reactions:
3030

