ምሩቃን በቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ስራ ፈጣሪ ዜጋ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ምሩቃን በቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ስራ ፈጣሪ ዜጋ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

ሆሳዕና ፤ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ) ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ስራ ፈጣሪ መሆን እንደሚጠበቅባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መዝረዲን ሁሴን ገለጹ።
የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለ17ኛ ዙር ከደረጃ አንድ እስከ አራት ያሰለጠናቸውን ከ630 በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
አቶ መዝረዲን ሁሴን በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከስራ ጠባቂነት አመለካከት የወጡ በራሳቸው ስራ ፈጥረዉ የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን ለማፍራት የተቋቋሙ ናቸው ብለዋል።
በኮሌጅ ቆይታቸው በንድፈ ሀሳብና በተግባር የቀሰሙትን እውቀት በግልም ሆነ በማህበር ተደራጅተው ከራሳቸው አልፈው ለሀገር የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ማስቻል በመሰረታዊነት ከተቋማቱ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እዉቀትና ክህሎት በመጠቀም ስራ ፈጣሪ ታታሪ ዜጋ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
በዚህም ምሩቃን እንደሀገር የተጀመረው ዘርፈ ብዙ ለዉጥና ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ አሻራቸውን ማሳረፍ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አብድልዋሂድ መሀመድ በበኩላቸው ኮሌጁ በተለያዩ የሙያ መስኮች ከደረጃ አንድ እስከ አራት ያሰለጠናቸውን ከ630 በላይ ተማሪዎች ዛሬ ማስመረቁን ተናግረዋል።
በሰርቨይ፣ በልብስ ስፌት ሙያ፣ በአይሲቲ እንዲሁም በሌሎች ዘጠኝ ዘርፎች ትምህርታቸውን ተከታትለው ብቁ የሆኑ ምሩቃን በዛሬው ዕለት መመረቃቸውን ተናግረዋል ።
ምሩቃን በኮሌጅ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም በተለያየ የስራ መስክ በመሳተፍ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልፅግና መረጋገጥ የበኩላቸውን ማበርከት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል የተመረቀችው መቅደስ ጌታቸው ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት በቆይታዋ ብዙ ውጣ ውረዶችን ብታልፍም ለምረቃ በመብቃቷ ደስታ ተሰምቷታል።
በቆይታዋ ያገኘችውን ዕውቀት በመጠቀም ስራን በመፍጠር ራሷንም ሀገሯንም ለመጥቀም ዕቅድ እንዳላት ተናግራለች ።
የአመለካከት ለዉጥ ካልታከለበት መማር ብቻው ከስኬት አያደርስም ያለው ደግሞ ሌላኛው ተመራቂ ሙሌ አሊ ነው።
በመሆኑም በትምህርት ያገኘውን ዕውቀት ከስራ ጠባቂነት አስተሳሰብ በመውጣት የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ ለመለወጥ እንደሚሰራ ተናግሯል።
መስራትና መለወጥ ለሚፈልግ ሰዉ መጀመሪያ የቀሰመውን ዕውቀት የሚተገብርበትን አማራጭ መፈለግ ሲቀጥል ደግሞ ተስፋ ሳይቆርጥ መተግበር ይገባል ነው ያለው
በ1990 ዓ.ም የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረው የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በእስከአሁኑ ሂደት ከ30 ሺህ በላይ ዜጎችን አሰልጥኖ ማስመረቁን ከኮሌጁ የተገኘው መረጃ ያሳያል።