በኢትዮጵያ ያሉ ተፋሰሶችን ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ ማልማት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ያሉ ተፋሰሶችን ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ ማልማት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ) ፦ መንግስት በኢትዮጵያ ያሉ ተፋሰሶችን ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ ማልማት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ ንዑስ ተፋሰስ ያለውን የውሃ ሃብት ማልማትና መጠበቅ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት እያካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ በውሃ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ የፌዴራል እና የክልል ተቋማት አመራሮች እና ባለሙያዎች እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ባሉ ተፋሰሶች የሚገኙ የውሃ ሀብቶችን በፍትሐዊነት፣ በዘላቂነትና በተቀናጀ መልኩ ለማልማትና ማስተዳደር የሚያስችሉ ተግባራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የተፋሰሶችን ደህንነት ጥበቃና የውሃ ሀብት አስተዳደርን መሰረት በማድረግ የተፋሰስ አካባቢዎችን በአሳታፊነት ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም መጤ አረሞችንና በካይ ንጥረ ነገሮችን ማጥፋትና መከላከል ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።
በዘርፉ ጥናትና ምርምር የተደረገባቸው የውሃ ሀብት መረጃዎች በአገራዊ የመረጃ ቋት ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በውይይት መድረኩ በደንበል ሻላ ተፋሰስ የሚገኙ የውሃ ሃብቶችን ለመጠበቅና ለማልማት የተመሰረቱ የባለድርሻ አካላት የትብብር ማዕቀፎች ላይ ያሉ መልካም ተሞክሮችና ፈተናዎችን በመለየት የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚቀመጡም አስረድተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቀጣይ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የተፋሰሱ የውሃ ሀብት ደህንነት እንዲጠበቅና በጋራ እንዲለማ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ለዚህም ባለድርሻ አካላት በተፋሰሱ የሚገኙ ችግሮችን ለመፍታት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል።
የማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ከ14 ሺህ 400 በላይ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ 27 በመቶውን እንደሚሸፍን መረጃዎች ያሳያሉ።