ብሪክስ እና ኢኮኖሚያዊ ፀጋዎቹ - ኢዜአ አማርኛ
ብሪክስ እና ኢኮኖሚያዊ ፀጋዎቹ
በዚህ ባለንበት ዘመን የተለያዩ ሀገራት መንግስታት ያላቸው ኢኮኖሚያዊ አቅም እና እድገት ምንም ይሁን ምንም ወደተሻለ ኢኮኖሚያዊ የብልፅግና ደረጃ ማደጉን ለማረጋገጥ እና የህዝባቸውን የኑሮ ሁኔታ ለማዘመን ያስችላሉ ያሏቸውን ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን በመንደፍ እና በመተግበር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ፍላጎቶችና ጥረቶች ከማሟላት አንፃር የብሪክስ ሀገራት ፖሊሲዎች አጋዥ እና ደጋፊ ሆነው ብቅ ብለዋል፡፡ የብሪክስ አባል ሀገራት በዓለም ዓቀፍ ኢኮኖሚ ውስጥ የታዳጊ ሀገራት መልካም ወካይ ሆነው በመገኘት በማደግ ላይ ለሚገኙ የዓለማችን መንግስታት በር ከፋች ሚናን በመጫወት ላይ ናቸው፡፡
በተለይ እ.ኤ.አ በ2008 ተከስቶ የነበረው የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቀውስ በብሪክስ አባል ሀገራት ላይ ያደረሰው አሉታዊ ተፅዕኖ ካደጉት ሀገራት አንፃር ሲታይ አነስተኛ በመሆኑ ለዚህ ሚናቸው መጉላት የራሱ እንድምታ አሳርፎ አልፏል፡፡
የብሪክስ ጥምረት በዓለማችን ኢኮኖሚ ላይ ያለው ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም እንዲያድግ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በተለያዩ የገበያ ዘርፎች ላይ ያላቸው ድርሻ መጨመር፣ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ያላቸው መሆን፣ ዝቅተኛ የሰው ሀይል ጉልበት ዋጋ እና ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም መገንባታቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም የብሪክስ ሀገራት ጥምረት በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ አዳዲስ ተገዳዳሪ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መልካም ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡
ባለፉት አስርት ዓመታት ካደጉት ኢኮኖሚዎች አንፃር ሲታይ የዓለማችን ታዳጊ ሀገራት ፈጣን የሚባል ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማስመዝገብ ላይ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በዓለማችን ዓመታዊ የምርት መጠን (GDP)፣ ዓለም አቀፍ ንግድ እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ያላቸው ድርሻ እያደገ በመምጣት ላይ ነው፡፡ በዚህ ወቅትም ዋነኛውን ሚና እና ድርሻ የሚጫወቱት የብሪክስ አባል ሀገራት ናቸው፡፡
እነዚህ ሀገራት የጋራ የሆኑ መገለጫ ባህርያት ያሏቸው ሲሆን ከነዚህ መካከልም ከፍተኛ የሆነ የማደግ እምቅ አቅም ያላቸው መሆን፣ በዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያላቸው ተፈላጊነት እያደገ መምጣት፣ የዓለማችን ኢኮኖሚ አመራር ላይ ጫና የመፍጠር አቅማቸው መጎለበት እና ተቀራራቢ የሆኑ ብሄራዊ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ያሏቸው መሆን ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡
በዚሁ የተነሳ በጋራ በመሆን በዓለማችን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና መስተጋብሮች ዙሪያ ያላቸው ተደማጭነት እና ተፅእኖ የማድረስ አቅም ከፍ ለማድረግ የሚያስችላቸው ጥምረትን የመሰረቱ ሲሆን ጥምረቱም ለታዳጊ ሀገራት የተስፋ ጭላንጭል ያበራ ሊሆን በቅቷል፡፡
የብሪክስ ሀገራት ጥምረት ለታዳጊ ሀገራት ካስገኟቸው ጸጋዎች መካከል የመጀመሪያ ተደርጎ የሚወሰደው በተለምዶ የብሪቶን ውድስ ተቋማት ተብለው የሚጠሩት የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ የምዕራቡ ዓለም ፖለቲከኞች እና ምዕራባዊያን ሀገራት በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚያደርሷቸው አላስፈላጊ ኢኮኖሚያዊ እና የፖሊሲ ጫናዎችን ለመገዳደር የሚያስችላቸው አማራጭ ሀይል ማግኘታቸው ነው፡፡
በተለይም የኢኮኖሚ ቀውሶችን ከመፍታት ይልቅ የታዳጊ ሀገራት ችግሮችን በማወሳሰብ የሚታወቀው የዋሽንግተን ስምምነት ተብሎ የሚታወቀው የምእራቡ ዓለም የኢኮኖሚ ሪፎርም ቅድመ ሁኔታና አዲስ የኢምፔሪያሊዝም የቅኝ ግዛት መሳሪያ ካደረሰባቸው ጉዳት ለመላቀቅ የብሪክስ እውን መሆን ከሰማይ የወረደ መና ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር የብሪክስ ሀገራት የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት የኢንዳስትሪያላዜሽን (import substitution industrialization) ፖሊሲ በተሟላ መንገድ ለመተግበር ከብሪክስ አባል ሀገራት የሚገኘው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ትልቅ አጋዥ መሳሪያ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ከዚህ ባሻገር የብሪክስ አባል ሀገራት በታዳጊ ሀገራት የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ያደረጓቸው ድጋፎች እና ኢንቨስትመነቶች በተለይ የአፍሪካ ሀገራት ያሏቸው እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች እሴት በመጨመርና በተሻለ ዋጋ ለዓለም አቀፍ ገበያ የማቅረብ አቅማቸው እንዲጨምር የማይተካ ሚናን ተጫውቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከብሪክስ አባል ሀገራት የሚገኘው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ታዳጊ ሀገራት የኢንዳስትሪያላዜሽን ልምድና ተሞክሮ እንዲያገኙ፣ ኢኮኖሚያዊ መስካቸውንና መዋቅራቸውን እንዲያሰፉ (achive economic diversification) እና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኤክስፖርት ሸቀጦችን እንዲያመርቱ በማስቻል ላይ ነው፡፡
የብሪክስ አባል ሀገራት በታዳጊው ዓለም ውስጥ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲመዘገብ፣ የታዳጊው ዓለም ሀገራት ዜጎች ሀገራዊ ብልጽግናን በፍትሀዊነትና እኩልነት እንዲጋሩ፣ ፈጣን የሆነ የቴክኖሎጂ ዕድገት እንዲቋደሱ እና ፈጠራነት የተሞላበት ሀገራዊ ልማት እንዲያሳኩ መንገድ በመጥረግ ላይ ያሉ ሀገራት ናቸው፡፡ ለዚህም ሲባል በኢነርጂ ላይ ቀጣይነት ያለው መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ በማድረግ፣ አማራጭ የሀይል ምንጮች (ሀይድሮ ኤሌክትሪክ፣ ነፋስ፣ የፀሀይ ሀይልና ሌሎች) ላይ ኢንቨስት በማድረግ እና በቴሌኮሚኒኬሽንና ኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ዘርፉን በመደገፍ ታዳጊ ሀገራት በጠንካራ መሰረት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገትና የብሄራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ ስራ እንዲሰሩ የብርታት ምንጭ ሆነዋል፡፡
የብሪክስ ሀገራት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ፋይናንስ ስርዓት እና አስተዳደር ላይ እያደገ በመሄድ ላይ የሚገኝ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ የዓለማችን 40 በመቶ ህዝብ የሚገኝባቸው፣ 25 በመቶ የዓለማችንን የምርት መጠን የሚሸፍኑ እና 50 በመቶ የዓለማችን የኢኮኖሚ እድገት ባለቤቶች ለመሆን በቅተዋል፡፡ በመሆኑም በአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ኢንዳስትሪያላዜሽን ላይ ላቅ ያለ አወንታዊ ሚና የመጫወት እምቅ አቅም ያላቸውና በመጫወት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን መገንዘብ አስፈላጊነቱ የጎላ ነው፡፡
የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲዎችን እንዲከተሉ ትልቅ አርአያ ከመሆናቸው ባሻገር የፋይናንስ እና የፖለቲካ ድጋፍ ምንጭ በመሆን ያላቸው ድርሻም በተመሳሳይ መልኩ የሚታይ ነው፡፡ የብሪክስ ሀገራት በአፍሪካ የግብርና ዘርፍ ላይ የሚያደርጓቸው ኢንቨስትመንቶች አህጉሪቷ አፍሪካ በምግብ ራሷን ለመቻል እና ግብርናውን ለማዘመን የምታደርገውን ጥረት እያገዘ ይገኛል፡፡
ከዚህ አንፃር የብሪክስ አባል ሀገራት የግብርና ትብብርን በማጠናከር፣ ለረሀብ ተጋላጭ ለሆኑ አፍሪካዊያን ለምግብ አቅርቦት ያላቸው ተደራሽነትን ለማሳደግ በየሚያስችሉ ስትራተጂዎች ዙሪያ ድጋፍ በማድረግ፣የአየር ንብረት ትግበራው ላይ ያለውን ተጽዕኖ በመቀነስ፣ የአካባቢ አየር ጸባይ ለውጥ በአፍሪካ ግብርና ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመቀነስ፣ የግብርናና ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን በመገንባት እና በግብርና ዘርፍ ያለውን የመንግስትና የግል ዘርፍ አጋርነት (develop public-private partnerships in agriculture) በማጠናከር ዙሪያ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸው እንደማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ሀገራችን በቅርቡ የብሪክስ አባል ሀገር ሆና መመረጧ እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸውን ጥቅሞችን እንድታገኝ የሚያስችላት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ፣ ደህንነት እና ዲፕሎማሲ ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር የብሪክስ ጥምረት አባልነት ዘርፈ ብዙ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን እንድትጎናጸፍ የሚያስችል ፀጋ በመሆኑ መልካም ውጤቱንና ፍሬውን ለመቋደስ የመንግስት እና የሁሉንም ሀገራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተዋንያን ቅንጅት፣ ትብብር እና ጥበብ ይጠይቃል፡፡