የግብርና ምርት ውል አሰራር አዋጅ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በግብርና ልማት እንዲሰማሩ ምቹ እድል ፈጥሯል-ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርት ውል አሰራር አዋጅ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በግብርና ልማት እንዲሰማሩ ምቹ እድል ፈጥሯል-ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ) ፦ የግብርና ምርት ውል አሰራር አዋጅ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በግብርና ልማት እንዲሰማሩ ምቹ እድል መፍጠሩን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በኢትዮጵያ ከ1942 ዓ.ም ጀምሮ የግብርና ምርት ውል ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ቢሆንም የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ የሚጠበቀውን ውጤት አላመጣም።
ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን የግብርና ምርት ውል አሰራርን መሰረት በማድረግ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ውጤታማ መሆን መቻላቸው ይነገራል።
ለአብነትም የተለያዩ ፋብሪካዎች፤ የጨርቃጨርቅና የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ከአርሶ አደሮች ጋር በግብርና ምርት ውል ትስስር በማምረታቸው ከውጭ ይገባ የነበረውን ምርት መተካት መቻሉ በውጤታማ ተሞክሮነት ይነሳል።
ኩባንያዎችን ፍላጎት ካላቸው አርሶ አደሮችና ማህበራት ጋር የማስተሳሰር አላማ አድርጎ የተዘጋጀው የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1289/2015 ሰኔ 29/2015 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ዋና ስራ አስፈጻሚ ደረጀ አበራ፤ የግብርና ኢንቨስትመንት ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ምርት ውል አሰራር አዋጅ (Contract Farming) ትግበራን ጨምሮ በግብርናው ሌሎች አሰራሮችንም የመተግበር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
አርሶ አደሮችን ከምርት ፈላጊዎች ጋር በሕጋዊ መንገድ ለማስተሳሰር የወጣው አዋጅ እየተተገበረ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አዋጁ ለተዋዋይ ወገኖች ከሚሰጠው ጥቅም ባለፈ በግብርና ልማት ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ባለሃብቶች ቴክኖሎጂ፣ ሃብትና እውቀት በማሟላት ከአነስተኛ ይዞታ እስከ ሰፋፊ እርሻ ስራ ላይ እንዲሰማሩ የሚያደርግ መሆኑንም አብራርተዋል።
አዋጁ በወጣ አጭር ጊዜ ውስጥ በምርጥ ዘር ብዜት ላይ የተሰማሩ ሁለት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የግብርና ምርት ውል አሰራርን መሰረት አድርገው ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።
አዋጁ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ምቹ እድል እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።
ኢንቨስትመንትን በመሳብ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በተለይም አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ ወደ ገበያ ተኮር ልማት ለማሸጋገር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የግብርና ምርት ውል አሰራር አዋጅ ውጤታማነት የአምራች፣ የአስመራች፣ የሶስተኛ ወገንና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅት ወሳኝ መሆኑንም አክለዋል።