ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል የሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲጎለብት እድል የፈጠረ ነው- በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ) ፦የመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል  የሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲጎለብት እድል የፈጠረ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ ገለጹ።

''መደመር የዘመኑ አርበኝነት'' በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በጅግጅጋ ተካሄዷል። 

በመድረኩ የፌዴራልና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ ''በመደመር ሰጥቶ መቀበል'' በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።

መደመር ከተናጠል ጉዞ አላቆ በሕብረት ከፍ ማለትን ያሳየ፤ የአብሮነትና ትብብርን ዋጋ በሚገባ ያመላከተ እሳቤ መሆኑን አመልክተዋል። 


 

በዚህም አጋር ተብለው በገዛ አገራቸው የመወሰን መብት ተነፍገው የነበሩ  ክልሎች  እኩል የመሳተፍና የመወሰን ዕድል ማግኘታቸውን ጠቁመዋል። 

ባለፉት አምስት ዓመታት በመደመር ማዕቀፍ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሶማሌ ክልልና ሕዝብ ብዙ ማትረፋቸውንም ተናግረዋል። 

ለአብነትም በክልሉ ውስጥም ሆነ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመነጋገርና በመተባበር መፍታት መቻሉን ጠቅሰዋል። 

በትጥቅ ትግል ላይ ከነበሩ አካላት ጋር ጭምር  በመነጋገር ወደ አገራቸው እንዲገቡና በሀሳብ ትግል እንዲሳተፉ ከማድረግ ባለፈ በሰጥቶ መቀበል መንገድ አብሮ መስራት መቻሉንም ነው ያብራሩት።


 

ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን በየደረጃው ያለውን የክልሉን መዋቅር ተሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ ማጠናከር መቻሉንም ተናግረዋል። 

በዚህም በክልሉ መንግስትና ሕዝብ መካከል ጠንካራ ትስስር መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመደመር እሳቤ በመፍታት ክልሉን ሰላማዊ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት  ሕዝብን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲንሰራ እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም