የመደመር እሳቤ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በትብብር መስራትን የሚያበረታታ የአርበኝነት መንገድ ነው - አቶ ዛዲግ አብርሃ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በትብብር መስራትን የሚያበረታታ የአርበኝነት መንገድ ነው - አቶ ዛዲግ አብርሃ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ) ፦ የመደመር እሳቤ አገርና ሕዝብን ከመውደድ በተጨማሪ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በትብብር መስራትን የሚያበረታታ የአርበኝነት መንገድ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ''መደመር የዘመኑ አርበኝነት" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የውይይት መነሻ ጽሁፋ ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዛዲግ አብርሃ፣ አርበኝነት ከኢትዮጵያውያን ጋር የተሳሳረ እሴት መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደምት ኢትዮጵያውያን በአርበኝነት መንፈስ በትብብር ኢትዮጽያን ከጠላት ተከላክለው ነጻ አገር ማስረከባቸውን ጠቅሰው፣ የድላቸው መሰረትም ትብብር መሆኑን ተናግረዋል።
የመደመር እሳቤ አገር በቀል እንደ መሆኑ መጠን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሐቅና እሴቶች ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ከዚህ አኳያ መደመር አገርና ሕዝብን መውደድ እንዲሁም የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በትብብር መስራትን የሚያበረታታ የአርበኝነት መንገድ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በተደመረ አቅምና በአርበኝነት መንፈስ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማሸጋገር ላይ መነሳት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
አገር መውደድና አርበኝነትን በሁሉም የልማት መስኮች ተግባራዊ በማድረግ ሙሉ ማድረግ እንደሚገባም እንዲሁ።
ለዚህ ደግሞ ካለፉ ታሪኮቻችን መልካሙን ማስቀጠልና ከስህተቶቻችን ደግሞ ትምህርት መውሰድ ይገባል ነው ያሉት።
ኢዜአ መደመርን አስመልክቶ ዛሬ ያዘጋጀው ሶስተኛ የውይይት መድረክ ሲሆን ከዚህ ቀደም በመደመር ላይ ያተኮሩ ሁለት የፓናል ወይይቶችን ማካሄዱ የሚታወስ ነው።