ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን በመደመር ዕሳቤ የጋራ ቤታችን የሆነችው ሀገራችንን ከፍታ ማረጋገጥ ይገባናል--የህግ ምሁር ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያውያን በመደመር ዕሳቤ የጋራ ቤታችን የሆነችው ሀገራችንን ከፍታ ማረጋገጥ ይገባናል ሲሉ የህግ ምሁሩ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ ገለጹ።

''መደመር የዘመኑ አርበኝነት'' በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ የፌዴራልና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

''መደመርና የኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የህግ ምሁሩ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ፤ የኢትዮጵያን ከፍታ እውን ሊያደርጉ የሚችሉ አስተሳሰቦችና ሀብቶች በሁሉም አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ሆኖም እነዚህን አስተሳሰቦችና ሀብቶች በሚገባ ባለመጠቀማችን ''መንገዱን በውል የማያውቅ መንገደኛ'' ሆነን ቆይተናል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የነበሩ መንግስታት ሀገር በቀል ያልሆኑ ዕሳቤዎችን ከማንነታችን ጋር ባልተሳሰረ መንገድ ለመተግበር ሲሞክሩ እንደነበርም በአብነት ጠቅሰዋል።

መደመር ከዚህ የተለየ ዕሳቤና አካሄድን ይዞ መምጣቱን የገለጹት ምሁሩ፤ ትውልድ ያለፈበትን መንገድ በመቃኘት፣ የዛሬን በመፈተሽ፣ የነገ መዳረሻን በግልፅ ማስቀመጥ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።


 

በዚህም መደመር ለኢትዮጵያ ከፍታ መንገድ መጥረጉን ገልጸው፤ የፍረጃ አካሄድን ወደ ጎን በመተው ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ትኩረት የሰጠ አስተሳሳሪ ዕሳቤ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያውያን የጋራ ከፍታቸው ዋስትና የሆነውን የመደመር ዕሳቤ የበለጠ በህዝብ ውስጥ ማስረጽ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምንጮች ተደምረው ትልቅ ወንዝ እንደሚሆኑ ሁሉ ኢትዮጵያውያንም በመደመር ዕሳቤ የጋራ ቤታችን የሆነችው ሀገራችንን ከፍታ ማረጋገጥ አለብን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም