ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከብራዚል ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር ዕድል ይፈጥራል - አምባሳደር ዣንዲር ፌሔይራ ዶስ ሳንቶስ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከብራዚል ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር ዕድል ይፈጥራል - አምባሳደር ዣንዲር ፌሔይራ ዶስ ሳንቶስ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከብራዚል ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት በአዳዲስ የትብብር መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥር በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ዣንዲር ፌሔይራ ዶስ ሳንቶስ ተናገሩ።
አምባሳደሩ ለኢዜአ እንደገለጹት ብራዚልና ኢትዮጵያ በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።
በተለይም ሁለቱ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመው ለዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው የገለጹት።
ሁለቱ አገራት በግብርና ዘርፍ ላይ ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው ጠቁመው በስፖርት ዘርፍም ልምድ መለዋወጥ የሚያስችል አጋርነት መመስረታቸውን ተናግረዋል።
ይህ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይም የተጠናከረ መሆኑን በመግለጽ።
አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከብራዚል ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት በአዳዲስ የትብብር መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥር አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
ብሪክስ አዲስ የልማት ባንክ፣ የብሪክስ ቢዝነስ ምክር ቤትና የብሪክስ የሴቶች የቢዝነስ አጋርነት የመሰሉ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በውስጡ የያዘ መሆኑን አንስተው ይህም የግንኙነት አድማሱን ይበልጥ ለማስፋትና ለማጠናከር ዕድል እንደሚሰጥ ነው የገለጹት።
ይህም ሁለቱ አገራት በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በስፖርትና በሌሎችም መስኮች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በዓለም አቀፍ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ አገራት ድምጽ እንዲሰማ የሚደረገውን ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን ያግዛል ነው ያሉት።
በተለይም ዓለም አቀፍ ሕግን ያከበረ ሁሉን አቀፍ የባለ ብዙ ወገን ግንኙነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማጠናከር የሚደረገውን አዎንታዊ ጫና ያጠናክራል ብለዋል።
በተጓዳኝም የባለብዙ ወገን የፖለቲካና የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርም እንዲያደርጉ የሚደረገውን ግፊት ወደ ፊት በመግፋት አበርክቶው ትልቅ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በተለይም በደቡብ ለደቡብ የትብብር ማዕቀፍ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ለማስተሳሰር የሚደረገው ጥረትንም እንደሚያጠናክረው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያና የብራዚል የሁለትዮሽ ግንኙነት ከተጀመረ 70 ዓመታትን አስቆጥሯል።