የመደመር እሳቤ በተሰናሰለ አቅም አገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የምናሸጋግርበት የአብሮነት መንገድ ነው--የሱማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ በተሰናሰለ አቅም አገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የምናሸጋግርበት የአብሮነት መንገድ ነው--የሱማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ) ፡- የመደመር እሳቤ በተሰናሰለ አቅም አገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የምናሸጋግርበት የአብሮነት መንገድ ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጋር በመተባበር ''መደመር የዘመኑ አርበኝነት'' በሚል ኃሳብ በጅግጅጋ ከተማ የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው።
በመድረኩም የሶማሌ ክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የመደመር እሳቤን መሰረት ያደረጉ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት የሚደረግባቸው ይሆናል።
በዚህ ወቅት የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ መልዕክትን ያቀረቡት በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌ፣ የመደመር እሳቤ አገርን እንዴት በትብብር ማሳደግ እንደሚቻል መንገድ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ኃሳብን ለጥላቻ ሳይሆን ለመረዳዳትና ለማደግ ማዋል እንደሚገባ አሳይቶናል ነው ያሉት።
ከዚህ አኳያ ልዩነቶችን በግጭት እንዲሁም ፍላጎትን በኃይል ለመጫን መሞከር አፍራሽ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ አፍራሽ አካሄድ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለከፋ ችግር እንደሚዳርግ ጠቅሰው፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት አገርን በትብብር ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሻገር ይገባል ነው ያሉት።
የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን ከውጭ ከሚመጣ የፖለቲካ ርዕዮት ጥገኝነት ያላቀቀ የእኛ የኢትዮጵያውያን መንገድ ነው ብለዋል።
ኢዜአ የመደመር እሳቤን መሰረት ያደረጉ የፓናል ውይይት በማዘጋጀት ዜጎች በኃሳቡ ላይ እንዲወያዩ እያከናወነ ያለውን ሥራም አድንቀዋል።
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሶማሌ ክልል የተገኙ ድሎችን እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ አዜአ እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።