መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እየሰራ ነው--ዶክተር ፍጹም አሰፋ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እየሰራ ነው--ዶክተር ፍጹም አሰፋ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ)፡- መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።
ዶክተር ፍጹም ከኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (KOICA) እና ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት (GGGI) ተወካዮች ጋር በጽህፈት ቤታችው ተወያይተዋል።
በውይይቱ የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ፕሬዝዳንት እና የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር ኪም ጂ ሂ፣ የኮይካ ዋና አማካሪ ሆንግ ሊል ፖ፣ በኢትዮጵያ የኮይካ ፕሮግራም አማካሪ ቤቴል ተረፈ እና የአለም አቀፍ አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ተወካይ ሶንግ ፊል-ጉን እንዲሁም የዓለም አቀፍ አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ በከተሞች አካባቢ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ተፈጥሮን መሰረት ያደረጉ መፍትሔዎች ለመጠቀም በሚያስችል ፕሮጀክት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
የከተማ አረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን ማጎልበትና የአየር ንብረት ለውጥን ማሳደግ የፕሮጀከቱ ዋና አላማ ሲሆን በውይይቱ የፕሮጀክቱን አዋጭነትና የትግበራ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ምክክር ተደርጓል።
ፕሮጀክቱ ከተለያዩ አገራዊ የልማት ማዕቀፎች ጋር በተለይም ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ(CRGE)፣ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድና ሌሎች ማዕቀፎች ጋር አብሮ ሊሄድ እንደሚችል ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የኘላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ከአየር ንብረት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ተቋሙ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲና የዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ተወካዮች ፕሮጀክቱ የከተማ አረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን ለማሻሻልና የአየር ንብረትን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ በተመረጡ የኢትዮጵያ ከተሞች እንደሚተገበር ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በዋናነት በከተማ ነዋሪዎች ላይ እንደሚያተኩርና ስነ-ምህዳሩን ወደ ነበረበት በመመለስ የደን ልማት፣ የደን መልሶ ማልማት እና ሌሎች ተያያዥ ለሆኑ ጉዳዮች ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ መፍትሄን ተግባራዊ ያደርጋል ተብሏል።
በዚህም ፕሮጀክቱ የአካባቢ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ አመልክተዋል።
ፕሮጀክቱ 6 ዓመታት እንደሚፈጅና በአዲስ አበባና በጅማ ከተሞች እንደሚተገበር ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።