ቀጥታ፡

የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ችግራችንን ማቃለል አስችሎናል -  በደቡብ ወሎና በምዕራብ ጎንደር  ዞኖች  ተጠቃሚዎች

ደሴ/ መተማ፤  ነሐሴ 27 /2015 (ኢዜአ)፡- በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት   ወጣቶች ባደረጉላቸው  ድጋፍ   ችግራቸውን ማቃለል እንዳስቻላቸው  በደቡብ ወሎና  በምዕራብ ጎንደር ዞኖች  አስተያየታቸውን የሰጡ  የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች  ገለጹ።  

በዘንድሮ የክረምት ወቅት በሁለቱ ዞኖች ከ479 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ተሰማርተው እየሰሩ እንደሚገኙ የየዞኖቹ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያዎች አስታውቀዋል።

ወይዘሮ በላይ ይመር በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ የሱሉላ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ቤታቸው አርጅቶ በክረምት በዝናብ፣ በበጋ ደግሞ በፀሐይና በንፋስ ሲቸገሩ እንደቆዩ ተናግረዋል፡፡


 

''ዘንድሮ በክረምት በጎ ፈቃደኞች ቤቴ በአዲስ መልኩ ተሰርቶልኝ ከችግሩ በመላቀቄ ተደስቻለሁ፣ አመሰግናለሁም'' ብለዋል፡፡

በአንድ ሄክታር ተኩል ማሳ ላይ ያለሙት ሰብል በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከአረም እንደጸዳላቸው የገለጹት ደግሞ በአልብኮ ወረዳ የ015 ቀበሌ አርሶ አደር ሐሰን ኢብራሂም ናቸው። 

"እንዲህ ዓይነቱ የመረዳዳት ባህል ተጠናቅሮ እንዲቀጥል ሁላችንም መስራት ይኖርብናል" ያሉት አርሶ አደሩ፤ ሰብሉ በአረም ተወሮ ከምርት ውጪ ይሆንብኛል ብለው ሰግተው እንደነበር አውስተዋል።

የወረዳው   ነዋሪ ወጣት ሰይድ ሁሴን በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከጓደኞቹ ጋር እየተሳተፈ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ከመስራት ባለፈ አርሶ አደሮችን  እያገዙ እንደሚገኙ ተናግሯል።

እስካሁንም የአራት አቅመ ደካሞች ቤቶችን ከመስራታቸው ሌላ ወላጆቻቸውን ያጡ  የስድስት  ልጆችና አቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ሰብል ከአረም ማጽዳታቸውን ተናግሯል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ምስጋናው ደምሴ በበኩላቸው ፤ በዞኑ ከ404 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


 

በአገልግሎቱ እስካሁን  239 የአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤት ጥገናና አዲስ ግንባታ፣ 58 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ፣  ደም ልገሳ፣ የ3 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህልና አልባሳት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም 732 ሄክታር የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች መሬት በመስመር ዘር ተሸፍኗል፣ 448 ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል ደግሞ ከአረም ጸድቷል ብለዋል፡፡

እስካሁን በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችም ከ687 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


 

በደቡብ ወሎ ዞን እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚቀጥለው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ አቶ ሙላው አብራራው እንዳሉት፤  በወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት   ቤት ተሰርቶ የተሰጣቸው ከመሆኑ ባሻገር ለ3 ወር የሚሆን የ50 ኪሎ የምግብ እህል ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አቅመ ደካማ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ባደረጉላቸው ድጋፍ ያልነበራቸውን መጠለያና ቀለብ ተመቻችቶላቸው ችግራቸውን ማቃለል እንደቻሉ ገልጸዋል።

ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና  አቅርበዋል።

በመተማ ወረዳ የኩመር አፍጥጥ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ውብነሽ አየነው በበኩላቸው ፤ በአንድ ሄክታር መሬት የለማ የማሽላ ሰብል በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከአረም እንደጸዳላቸው ተናግረዋል።

"ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ባያርሙልኝ ኑሮ ሰብሉ ጥቅም አልባ ይሆን ነበር" ያሉት ወይዘሮዋ፤ አሁን ሰብሉ ባለው ቁመና ከራሳቸው ምግብ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ችግራቸውን እንደሚፈታላቸው አስረድተዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የወጣቶች ዘርፈ ብዙ ማካተት ቡድን መሪ አቶ ሀይለየሱስ መኮንን እንዳስታወቁት፤ በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ ስራ ላይ 75 ሺህ ወጣቶችን እየተሳተፉ ይገኛል።

''በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ሀሳብ  እየተካሄደ ባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ340 በላይ የቤት ክዳን ቆርቆሮ በማሰባሰብ 112 የመኖሪያ ቤቶችን በአዲስ የመገንባትና የመጠገን ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

እንዲሁም ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ 1 ሺህ 610 የሚሆኑ ሰዎችን የማዕድ የማጋራት መረሃ ግብር መካሄዱንም ጠቅሰዋል።

ወጣቶቹ የ400 ሺህ ችግኝ ተከላ፣ 1 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የጎርፍ ማፋሰሻ  ማፅዳት፣ 18 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ጥገና፣ የትምህርት ቤት ጥገና የደም ልገሳና የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠታቸውን አመልክተዋል።

ወጣቶች የሚሰጡት አገልግሎት መቀጠሉንና እስካሁን 28 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት መስጠት መቻሉን አስረድተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም