የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቀጣዩ ዓመት በበይነ መረብ ግብይት ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቀጣዩ ዓመት በበይነ መረብ ግብይት ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቀጣዩ ዓመት ተገበያዮች ባሉበት ቦታ ሆነው ግብይታቸውን የሚያከናውኑበት የበይነ መረብ ግብይት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
ግብይቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን የዲጂታል ስትራቴጂ መሰረት ለማድረግና የግብይት ስርዓቱን ተደራሽነት ለማስፋት መሆኑ ታውቋል።
በዚህም አምራቹ፣ አቅራቢና ላኪዎች ካሉበት ቦታ ሆነው በኦንላይን በቀላሉ ግብይት መፈጸም የሚችሉ ይሆናል።
የበይነ-መረብ ግብይት ማስተግበሪያ ሶፍትዌር ፕሮጀክት (Online Trading Project) በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት ተነድፎ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት አማካኝነት መበልጸጉን ምርት ገበያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።
ግብይቱን ለማስጀመር የዝግጅት ምዕራፉን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
በተጨማሪ ተገበያዮች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የግብይት ትዕዛዞቻቸውን ማስገባትና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና መስሪያ ቤት ወይም የቅርንጫፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ሳይመጡ ከግብይት ጋራ በተያያዘ የሚፈልጓቸውን መረጃዎች ማየት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
የግብይቱ ሂደት ደህንነቱ የተጠበቀና ሙሉ በሙሉ ከሰው ንክኪ ነጻ በሆነ መልኩ የሚተገበር መሆኑንም መግለጫው አመለክቷል።