ቀጥታ፡

ለበዓሉ በምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል -  የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 26/2015 (ኢዜአ) ፡- የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ 

ለበዓል ገበያ  በሁሉም አካባቢዎች የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይገጥም እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ በሰጡት መግለጫ፤ የዘመን መለወጫ በዓል ላይ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር በርካታ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዋጋ ንረት እና ህገ-ወጥ ንግድን በመቆጣጠር የተረጋጋ የገበያ እንቅስቃሴ እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡም ይህንኑ ተገንዝቦ መገበያየት እንዳለበት አስገንዝበዋል። 

ከበዓል ጋር በተያያዘ ምንም አይነት የምርት አቅርቦት እጥረት አይገጥምም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የግብርና ምርቶችም ይሁን የእርድ እንስሳት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለገበያ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በግብይት ወቅት በምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ምርቶችን በመጋዘን በሚያከማቹ ነጋዴዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 


 

የኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ቀፀላ ሸዋረጋ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ለበዓል ፍጆታ የሚውል የዘይት ምርት አስገብቶ ወደ ሁሉም አካባቢዎች በማሰራጨት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የፓልም ዘይት ባለ 3 ሊትር ዘይት 324 ብር ፣ ባለ 5 ሊትር 526 ብር፣ እንዲሁም ባለ 20 ሊትር በ2ሺ64 ብር ለገበያ ቀርቦ በመሸጥ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

የዋጋ ንረት እና ህገ-ወጥ ንግድን በመቆጣጠር የተረጋጋ የገበያ እንቅስቃሴ እንዲኖር ህብረተሰቡ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም