ቀጥታ፡

​​​​​​​የዜጎችን ህይወት ከትራፊክ አደጋ ለመታደግ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፋችን የህሊና እረፍት አግኝተናል- በጎ ፈቃደኞች

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 26/2015 (ኢዜአ) ፡-የዜጎችን ህይወት ከትራፊክ አደጋ ለመታደግ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፋችን የህሊና እረፍት እንድናገኝ አድርጎናል ሲሉ የአዲሰ አበባ በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተባባሪዎች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በበኩሉ በጎ ፈቃደኞቹ የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥ አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጿል።

ኢዜአ የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው ሜክሲኮ አደባባይና አስኮ አካባቢ የሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተባባሪዎችን አነጋግሯል።

የሜክሲኮ አካባቢ በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ ፍሰት አስተባባሪ ፈድሉ በርጋ፤ በትራፊክ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ8 ዓመት በላይ ማገልገሉን ገልጿል።

አገልግሎቱም የትራፊክ እንቅስቃሴን በማሳለጥ ዜጎች ለአደጋ እንዳይጋለጡ፣ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይም ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን በመታደግ የህሊና እርካታ እያገኘ መሆኑን ገልጿል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በፍላጎት እና በራስ ተነሳሽነት የሚከናወን መልካም ተግባር ነው ያለችው ደግሞ፤ ሌላኛዋ የአስኮ አካባቢ የትራፊክ አስተባባሪ ወጣት እመቤት በቀለ ናት።

የተሽከርካሪ ፍሰትን ለማሳለጥ፣ ዜጎች በዜብራ እንዲሻገሩ በማድረግ፡ የስርቆትና የትራፊክ አደጋ ቅድመ መከላከል ስራ በማከናወን ደስታ የሚቸራትን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠች መሆኗን ገልፃለች።

በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተባባሪው ወጣት ሚፍታህ ከድር እንደሚለውም የተሽከርካሪና የሰዎች ፍሰት በሚጨምርበት ከጥዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ 4፡30 ድረስ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠን  ነው ብሏል።

''ካለኝ የእረፍት ሰዓት ቀንሼ አረጋውያንን ፣ነፍሰጡር እናቶችና አካል ጉዳተኞች ከመኪና አደጋ በመታደጌ ተደስቻለሁ'' ሲልም አክሏል።

ወጣት ፈድሉ በርጋ በበኩሉ ዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህላችንን በማዳበር የመደጋገፍና የመረዳዳት ኢትዮጵያዊ ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል ብሏል። 

በተለይ ወጣቶች የእረፍት ጊዚያቸውን በአልባሌ ቦታ ከሚያሳልፉ  በበጎ ስራ ላይ ቢያውሉት ፣ ወገናቸውን ከአደጋ መታደግ ይችላሉ ነው የሚለው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ መኳንንት ምናሴ፤ በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪዎችን አሰልጥኖ በማሰማራት የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት የተሳለጠ እንዲሆን እያደረገ ነው ብለዋል። 

በመዲናዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከ600 በላይ መደበኛ በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተባባሪዎችም ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት በሚስተዋልባቸው ቦታዎች ተገኝተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የበጎ ፈቃደኞቹ አገልግሎትም ዜጎች ለትራፊክ አደጋ እንዳይጋለጡ ፣አሽከርካሪዎች ህግና ሥርዓት አክብረው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም