ቀጥታ፡

ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጠናከረ ቁጥጥር እየተደረገ ነው-የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 26/2015 (ኢዜአ) ፦ ከበአል ጋር ተያይዞ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።

የ2016 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በአልን ለማክበር አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ከወዲሁ ግብይት እየተካሄደ ይገኛል።

የግብይት ሂደቱን ተጠቅመው ለወንጀል ተግባራት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን በመከታተልና በመቆጣጠር በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል።

የባለስልጣኑ የምግብ አምራች ተቋማት ኢንስፔክተር አየነው አንዳርጌ፤ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ለበዓል ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ነው።

ለበዓሉ በብዛት ግብይት በሚካሄድባቸውና ምርት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የጥራት ቁጥጥር በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራው በቅንጅት መካሄዱ ቀጥሏል ብለዋል።

ህብረተሰቡ የሚሸምታቸውን ምርቶች በጥንቃቄ በማየት ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ አየነው፤ በተለይም ትኩረትና ጥንቃቄ ይሻሉ ያሏቸውን ምርቶች ጠቅሰዋል።

በየአካባቢው ለገበያ በሚቀርቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን በጥንቃቄ በማየት መግዛት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በግብይት ወቅት አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙም በባለስልጣኑ ነፃ የስልክ መስመር 8482 ማሳወቅ ወይም ለጸጥታ አካላት መረጃ መስጠት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም