አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 26/2015 (ኢዜአ) ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎችና በተለይም በአማራ ክልል ስላለው የሰብዓዊ ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት አጠቃላይ የሰብዓዊ ሁኔታው እንዲሻሻልና ከረድኤት ድርጅቶች ጋር በመሆን ምግብን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች ተደራሽ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ በአማራ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በሰጡት ማብራሪያ የክልሉ አካባቢዎች መሰረታዊ አገልግሎቶች መጀመራቸውን አመልክተዋል።
የረድኤት ድርጅቶች አስቸኳይ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች የሚያደርጉትን ድጋፍ በአፋጣኝ ሙሉ በመሉ እንዲጀምሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የተመድ የሰብአዊ ድርጅቶች ተወካዮች መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶችን አድንቀዋል።
በውይይቱ ተወካዮቹ የምግብ እርዳታ የመጀመርን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው ማንሳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።