የጌደኦ ዞን ወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጥረቶች እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጌደኦ ዞን ወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጥረቶች እየተደረጉ ነው
ዲላ ፤ ነሐሴ 26/2015 (ኢዜአ) የጌደኦ ዞን ወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና የዞኑ ስራ ኃላፊዎች ገለጹ።
በዞኑ "ለአካታች ሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ለዘላቂ ሠላምና ብልጽግና የወጣቱ ሚና" በሚል መሪ ቃል አምስተኛው የወጣቶች የውይይት መድረክ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የዞኑን ወጣቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ነው።
የዞኑን የመልማት አቅሞች በመለየት በተለይ በከተማ ግብርና፣ በዶሮና እንስሳት እርባታ እንዲሁም ፍራፍሬና ቡና ችግኝ ማፍላት ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በዘርፎቹ ተደራጅተው ስራ ለሚፈጥሩ ወጣቶች አስፈላጊውን የመስሪያ ቦታና የመነሻ ሀብት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዞኑ ተጀምረው ያላለቁ ትላላቅ የመንግስትና የግል ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን አቶ አብዮት ገልጸዋል።
በዞኑ ሁሉን አቀፍ እድገት ለማረጋገጥ የጋራ ጥረት ይጠይቃል ያሉት ኃላፊው፣ ወጣቶች ከአስተዳደር አካላት ጋር በመቀናጀትና በመደጋገፍ እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ዞኑ ለሰላም ግንባታና ለዘላቂ ልማት የወጣቶችን ተሳትፎ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ተወልደ ተስፋዬ ናቸው።
የወጣቶች የልማትና የተሳትፎ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተቀናጀ ጥረት እንደሚደረግ ጠቅሰው፣ ወጣቱ ዞኑን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር አሳስበዋል።
በተለይ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም ሀገራዊ፣ ክልላዊና ዞናዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመረዳት ለችግሮች መፍትሄ እንዲያፈላልጉ አስገንዝበዋል።
በኮንፍረንሱ የተሳተፉ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት በዞኑ የወጣቶች እኩል ተጠቃሚነትና ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት አመልክተው፣ በተለይም በስራ እድል ፈጠራ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ተፈተው ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ጠይቀዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ወጣት ክብሩ ዶጌ እንዳለው የወጣቶችን ጥያቄ ሰምቶ ምላሽ ለመስጠትና የጋራ መግባባት ለመፍጠር መድረክ ማዘጋጀቱ የሚበረታታ ነው።
በዞኑ አዋጭ የስራ ዘርፎች ተለይተው ወጣቱ ተደራጅቶ ወደ ስራ ለመግባት የሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጣቸው በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብሏል።
በዞኑ የዲላ መካከለኛ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በርካታ የግልና የመንግስት ተቋማት ተገንብተው ወደ ስራ አለመግባታቸው የወጣቱን ስራ የማግኘት እድል መቀነሱን ያነሳችው ወጣት ልደት እንግዳየሁ ናት።
ይህም ከቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ከሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የወጡ ወጣቶች በስራ ተሰማርተው ልምድና ክህሎት እንዳይቀስሙ ማድረጉን ገልጻለች።
''እኛም የዞኑ ልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ እንደከዚህ ቀደሙ የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል'' ብላለች።
ወጣት ሃብታሙ ገልፈቶ በበኩሉ ወጣቱ የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ያደረገውን ተሳትፎ በልማት ለመድገም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
መንግስት ከወጣቱ ጋር ለመወያየት እድል ማመቻቸቱ በቀጣይ ችግሮችን ለመፍታት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቆ፣በወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ተቀናጅቶ እንደሚሰራም ገልጿል።