ቀጥታ፡

ለበዓል ገበያ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር ምርቶች በብዛት ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ነው- የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2015(ኢዜአ)፡- ለበዓል ገበያ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በብዛት ወደ አዲስ አበባ እየገቡ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ሊፈጠር የሚችል ሕገወጥነትን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይል ወደ ስራ ገብቶ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑም ተገልጿል። 

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሰውነት አየለ፤ ለበዓል ገበያ ምርቶችንና የእርድ እንስሳትን ጭምር በብዛት ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ምርቶች፤ የእርድ እንስሳትና ሌሎችንም አቅርቦት በተመለከተ ከተማ አስተዳደሩ በክልሎች ከሚገኙ አምራች ዩኒየኖች የምርት ትስስር  ውል ተፈራርሞ በማስገባት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠርም ለበዓል ከ1 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ለሸማቾች የሚቀርብ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

ህብረተሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኝባቸው የተለያዩ የገበያ አማራጮች መዘጋጀታቸውን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በሚዲናዋ በ172 የእሁድ ገበያዎች፣ በ152 የሸማቾች ማህበራት እና 7 ትላልቅ የገበያ ማዕከላት የተለያዩ ምርቶች በብዛት መቅረባቸውን ጠቁመዋል።

ከነገ ጀምሮ እስከ በዓሉ መዳረሻ ድረስ በመዲናዋ በ25 የተለያዩ አካባቢዎች በሚካሄዱ ኤግዚቢሽኖች ምርቶችን ማግኘት ይችላሉ ብለዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የተለያዩ ተቋማትን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቋሞ ወደ ስራ መግባቱንም ገልጸዋል።

በአዲሱ ገበያ ሕብረት ስራ ማህበራት እና በአራዳ የብርሃን ለሕዝብ የሕብረት ስራ ማህበር ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ አስናቀች ጌታቸው እና ወይዘሮ እሰየ ማስረሻ፤ ለበዓል የምርቶች አቅርቦት በተለያየ አማራጭና በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረቡን ገልጸዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 የብርሃን ለሕዝብ የሕብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ይታየው ታደለ፤ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ጭምር ለበዓል ገበያ በብዛትና በስፋት መቅረባቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ በሕብረት ስራ ማህበሩ በኩል የሚቀርቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዲሱ ገበያ ኃላፊነቱ የተወሰነ ሕብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ ሞገስ መንገሻ፤ ጥራታቸው የተጠበቁ በቂ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

ከበዓል ጋር ተያይዞ አንድ ኪሎ ግራም የስንዴ ዱቄት በ78፣ ጤፍ ከ69 እስከ 91 ብር፣ ቡና በ360 ብር እንዲሁም እንቁላል በ10 ብር ለሸማቾች ቀርቧል ብለዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም