ቀጥታ፡

አምባሳደር ጀማል በከር የፓኪስታን የሰላም ሽልማት ተበረከተላቸው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 26/2015 (ኢዜአ) ፡- በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር የኢትዮጵያና ፓኪስታን የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጎልበት ባደረጉት አስተዋጽኦ የፓኪስታን የሰላም ሽልማት ተበረከተላቸው።

በተያያዘም በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ የ”2023 ምርጥ አምባሳደር ሽልማት” ከኮሪያ የሸማቾች ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ተበርክቶላቸዋል።
 

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል ሽልማቱ የተበረከተላቸው ከፓኪስታን ብሔራዊ የሰላምና ፍትሕ ምክር ቤት ነው።

የምክር ቤቱ ሊቀ መንበር ሚያን አብዱል ለአምባሳደሩ ሽልማቱን አበርክተዋል።

አምባሳደር ጀማል የፓኪስታን መንግስት የኢትዮጵያና ፓኪስታን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለማጠናከር ላደረጉት ሁሉን አቀፍ ጥረት ለሰጣቸው እውቅና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሁለቱ አገራት በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በተያያዘም በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ የ”2023 ምርጥ አምባሳደር ሽልማት” ከኮሪያ የሸማቾች ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ተበርክቶላቸዋል።

አምባሳደር ደሴ ሽልማቱን ያገኙት ሁለቱ አገራት በኢንቨስትመንት፣ በንግድና ትምህርት ያላቸው ትብብር እንዲጎለብት ላደረጉት አስተዋጽኦ እንደሆነም ተገልጿል።

በተለይም በሁለቱ ወዳጅ አገራት መካከል ያለው የኢንቨስትመንትና የባህል ልውውጥ እንዲጎለብት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ፎረሞችን በማዘጋጀት ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ምክር ቤቱ ገልጿል።

አምባሳደር ደሴ ሽልማቱ የሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ይበልጥ ለማስተሳሰር ለሚያከናውኑት ስራ ተነሳሽነት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር አበክረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም