ከተለያዩ ተቋማት ለተወጣጡ ከ3 ሺህ 600 በላይ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና ተሰጥቷል - የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
ከተለያዩ ተቋማት ለተወጣጡ ከ3 ሺህ 600 በላይ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና ተሰጥቷል - የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ ነሐሴ 25/2015 (ኢዜአ)- በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት የተቋማትን የምርትና የጥራት ደረጃ ለማሻሻል ከተለያዩ ተቋማት ለተወጣጡ ከ3 ሺህ 600 በላይ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና መስጠቱን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ ደረጃዎችን እንዲያዘጋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ዓለም አቀፍ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ያላቸውን ደረጃዎች በየጊዜው ያጸድቃል።
ከዚህም በተጨማሪ በኢንስቲትዩቱ ሥልጠና አካዳሚ የሥልጠና፣ የማማከርና የቴክኒክ ድጋፎችን በመስጠት ተቋማት በምርት ጥራት ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ ከ46 ተቋማት ጋር የሥልጠናና የቴክኒክ ድጋፎችን ለመስጠት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርሟል።
ይህንንም ተከትሎ የተቋማት የምርት ጥራት እንዲጨምርና በደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑም ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው የሥልጠና ማዕከሉ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በ2015 በጀት ዓመትም ከ3 ሺህ 600 በላይ ለሆኑ የተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።
ሥልጠናው በመልካም ሥራ አመራር፣ በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት፣ በምግብ ደኅንነት፣ በአካባቢ ደህንነትና በሌሎችም ተያያዥ ዘርፎች ትኩረት አድርጎ መካሄዱን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ተቋማቱ የቅሬታ አፈታት ሥርዓታቸውን እንዲያሻሽሉና ዘመናዊ የመዝገብ አያያዝ ሥርዓት እንዲዘረጉም ጭምር የቴክኒክ ድጋፎችን እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።
ጎን ለጎንም በተለያዩ ክልሎች ከ1 ሺህ 600 በላይ ለሆኑ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋም ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን መስጠቱንም ጠቅሰዋል።
ኢንስቲትዩቱ የሚሰጣው ሥልጠናና የቴክኒክ ድጋፉ ተቋማት የምርት ጥራት ደረጃ እንዲሁም አጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ በሚሰጠው ዓለም አቀፍ ሥልጠና፣ የቴክኒክ ድጋፍና የማማከር አገልግሎት ተቋማት ለዓለም አቀፍ የጥራት ድርጅት (ISO) የዕውቅና ሰርተፍኬት እንዲያገኙ የማብቃት ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
የብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት በተለያዩ የምርትና የአገልግሎት ዘርፎች 1 ሺህ 472 ደረጃዎች ማጽደቁ ይታወሳል።