ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊቱ ህግን ከማስከበሩ በተጓዳኝ ለልማት እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ ይቀጥላል- ሌተናል ኮለኔል በላይነህ በለጠ

ደሴ ፤ ነሐሴ 26 ቀን 2015 (ኢዜአ)፡- የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሕግን ከማስከበርና ሰላምን ከማስፈን በተጓዳኝ ለልማት እያደረገ ያለውን እገዛ  አጠናክሮ  እንደሚቀጥል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አባል ሌተናል ኮለኔል በላይነህ በለጠ ገለጹ።

መከላከያ ሰራዊቱ  በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን የሰብል ማሳ ከአረም የማፅዳት ስራ አከናውኗል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አባልና የአልብኮ ወረዳ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ኮለኔል በላይነህ በለጠ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ መከላከያ ሰራዊቱ ለግዳጅ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ሁሉ ህብረተሰቡን ያገለግላል፡፡


 

ሰራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበር  እያስከበር ግዳጁን በድል ከመወጣት በተጓዳኝ  አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ህዝባዊነቱን በተግባር የሚያረጋግጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን ገልጸዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ በአርሶ አደሮች ማሳ ተገኝቶ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ሰብል ከአረም የማጽዳት ሥራ ማከናወኑን ጠቅሰው፤ በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡም አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ  ደጀን ሆኖ ድጋፉን በማጠናከር  ለሰራዊቱ ያለውን ፍቅር በተግባር እያረጋገጠ መሆኑንም  ተናግረዋል፡፡

ከሰራዊቱ አባላት መካከል መሰረታዊ ወታደር ደሴ ግዛቸው በሰጡት አስተያየት፤  በአጥንትና በደማችን ሀገርና ህዝብ ከመጠበቅ በጉልበታችንና በገንዘባችን ህዝባችንን እያገለገልን እንገኛለን ብለዋል፡፡


 

ዛሬም የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች የሰብል ማሳ ከአረም የማጽዳት ስራ ማከናወናቸውን ጠቅሰው፤በቀጣይም ለሌላው ማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት አብሮነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

ሰብሉ ሲደርስም ለማጨድና ለመውቃት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ህዝባችን ከጎናችን ተሰልፎ ሁለተናዊ ድጋፍ በማድረግ ድጋፍ እየሰጠን ተጨማሪ አቅም ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደመቀ አድማሱ በበኩላቸው፤በዘንድሮው የመኸር ወቅት በዞኑ  ከ419 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ለምቶ የአረም ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

እስካሁን በ100 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል ከአረም መጽዳቱን ጠቁመው፤ ምርታማነትን ለማሳደግ ሰብሉን ከአረምና ተባይ የመጠበቅ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በተለይ መከላከያ ሰራዊቱ ህግ ከማስከበር ባለፈ የአቅመ ደካሞችን ሰብል ከአረም በማጽዳት ህዝባዊነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

አቅመ ደካማ በመሆናቸው በመኽር ወቅቱ በአንድ ሄክታር ማሳ ያለሙት ጤፍና ገብስ በአረም ተወሮ የቆየውን መከላከያ ሰራዊቱ ባደረገላቸው ድጋፍ መጽዳቱን የገለጹት  በአልብኮ ወረዳ የ015 ቀበሌ አርሶ አደር ደርብ አራጋው ናቸው።


 

በዚህም  እፎይታ ማግኘታቸውንና  ለተደረገላቸው እገዛም ምስጋና አቅርበዋል።

ሰብልን ከአረም በማጽዳቱ ስራ ላይ ከመከላከያ ሰራዊቱ በተጨማሪ የደቡብ ወሎ ዞንና የአልብኮ ወረዳ አመራሮችም ተሳትፈዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ዘንድሮ በመኸር ከለማው መሬት 13 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከግብርና መምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም