የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን በሠለጠነ የሰው ኃይል በመምራት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው - የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን በሠለጠነ የሰው ኃይል በመምራት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው - የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2015(ኢዜአ)፦ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች በሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲመሩ በማድረግ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም ለኢዜአ እንደገለጹት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በርካታ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ነው።
በተለይም የመዳረሻ ሥፍራዎች በብቁ ባለሙያ መመራት በዘርፉ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ያግዛል ብለዋል።
ይህም ዘርፉ ለአገራዊ አጠቃላይ ምርት የሚኖረውን ሚና ከማሳደግ በዘለለ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ሚናው የላቀ እንደሚሆን ነው የገለጹት።
ከዚህ አንጻር ኢንስቲትዩቱም አጫጭርና ረጃጅም ሥልጠናዎች በመስጠት ለዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በአደረጃጀትና በሰው ኃይል ግንባታና ተያያዥ ጉዳዮች የማማከር ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትም በጥናት ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ አቅጣጫ እያቀረበ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
ጎን ለጎንም የኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ ፕሮጀክቶች የሚፈጥሩትን የሥራ እድል ታሳቢ ያደረገ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከወዲሁ የማዘጋጀት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመጪው የትምህርት ዘመን በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የትምህርት ዘርፎችን በመለየት ጭምር ሥልጠና ለመስጠት መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ አሁን ላይ ወደ 2 ሺህ ለሚጠጉ ተማሪዎች በቀንና በማታ መርኃ ግብር ሥልጠና እየሰጠ መሆኑ ተገልጿል።