በሰሜን ሸዋ ዞንና ደብረብርሀን ከተማ አስተዳደር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ምዝገባ እየተካሄደ ነው-መምሪያዎቹ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞንና ደብረብርሀን ከተማ አስተዳደር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ምዝገባ እየተካሄደ ነው-መምሪያዎቹ

ደብረ ብርሀን ነሐሴ 25/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና በደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር በ2016 ትምህርት ዘመን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን የትምህርት መምሪያዎች አስታወቁ።
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ታደሰ ሸዋፈራ ኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ ከነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የ2016 ትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው።
ምዝገባው እስከ ጳጉሜ 3 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ ጠቁመው በዞኑ በትምህርት ዘመኑ በሁሉም የትምህርት እርከኖች 522 ሺህ ተማሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱን አመልክዋል ።
ለመመዝገብ ከታቀደው ውስጥ 68 ሺህ 530 የሚሆኑት አንደኛ ክፍል የሚገቡ አዲስ ተማሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተማሪዎች ምዝገባ በታሰበው ጊዜ እንዲከናወን ወላጆች በወቅቱ ልጆቻቸውን በማስመዝገብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በተመሳሳይ የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር በአዲሱ የትምህርት ዘመን 55 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ምዝገባ እያካሄደ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጥበቡ ገሰሱ ናቸው።
ከነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከዛሬ ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍል ጥበት፣ የመማሪያ መፅሃፍት እጥረትና መሰል ችግሮች በመፍታት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከወላጆች መካከል ወይዘሮ እመቤት ተድላ በሰጡት አስተያየት በአዲሱ የትምህርት ዘመን ሁለት ልጆቻቸውን ማስመዝገባቸውን ገልፀዋል።
ለምዝገባው በቂ ዝግጅት በመደረጉ መጉላላት ሳይኖር ማስመዝገብ እንደቻሉ ጠቅሰው ወላጆች ልጆቻቸውን በወቅቱ ማስመዝገብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ የአፄ ዘራያቆብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ጽዮን ዘበነ በበኩሏ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ለትምህርቷ ትኩረት ለመስጠት በማሰቧ ቀድማ መመዝገቧን ገልፃለች።
በክረምት ወቅቱ ተገቢውን ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷን አመልክታለች ።