18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ጠንካራ ህብረብሔራዊ አንድነትና ወንድማማችነትን በማጽናት መርህ ይከበራል--የፌደሬሽን ምክር ቤት

18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ጠንካራ ህብረብሔራዊ አንድነትና ወንድማማችነትን በማጽናት መርህ እንደሚከበር የፌደሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ምክር ቤቱ 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል መሪ ዕቅድ ላይ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሀላፊዎች ጋር በመወያየት አጽድቋል።

በየዓመቱ ሕዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን "ብዝሃነትና ዕኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ ከተማ እንደሚከበር ተገልጿል።

ከዋናው ክብረ በዓል በተጨማሪ ከሕዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ተመላክቷል።


 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር በኢትዮጵያ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር እንደሚያስችል ገልጸዋል።

18ኛው ዙር የበዓሉ አከባበር ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ስኬትና  ድል ባስመዘገበች ማግስት መከበሩ ለየት እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የብሔር ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕኩልነት እንዲረጋገጥ በመሰራቱ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መሆኑን አንስተዋል።

የሶማሌ ክልል በዓሉን ለማስተናገድ እያደረገ ያለው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አበረታች መሆኑን ጠቁመው፤ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን አገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የጉባዔዎች ዳይሬክተር አብዱልናስር አሬስ፤ ክልሉ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።


 

እስካሁንም ዓብይ እና ንዑስ ኮሚቴዎችን የማቋቋም፣ የእንግዶች ማረፊያ ልየታና የመንገዶች ጥገና ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

በውጭ አገራት የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የበዓሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ መደረጉን አንስተዋል።

 

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም