ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በአማራጭ ልማት ፋይናንስ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችላት ነው- የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በአማራጭ ልማት ፋይናንስ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችላት ነው- የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በአማራጭ ልማት ፋይናንስ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችላት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ተናገሩ።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በቅርቡ ብሪክስን መቀላቀሏ፣ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የሚያሳይ ጠንካራ መገለጫ ነው።
ቡድኑን ለመቀላቀል ጥያቄ ካቀረቡ 40 አገራት መካከል ይሁንታ ማግኘቷ የበሳል አመራርና የጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ከመንግስታቱ ድርጅት ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት በተጨማሪ ከሌሎች ፋይናንስ ተቋማት እና ከአገራት ጋር ግንኙነት በማጠናከር ከሁሉም ወገን ጋር በጋራ እንድትሰራ ያስችላታል።
ብሪክስም አማራጭ የልማት ፋይናንስ ምንጭና አቅም በመሆን የኢትዮጵያን የወደፊት ተስፋ የሚያለመልም እንደሆነም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አማራጭ የፋይናንስ ልማት ዕድሎችን ለመጠቀም ስትስራ መቆየቷን ጠቁመው፤ በቀጣይም ጥቅሟን ለማስከበር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ተቋማት ትልቅ ስምና ተጽዕኖ ያላት ሀገር በመሆኗ በብሪክስ ውስጥ ባገኘችው ዕድል ጥቅሟን ለማስጠበቅ እንደምትሰራም ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ በተደረገው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሀገራት ቡድኑን መቀላቀላቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ እና ግብጽ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ቡድኑን የተቀላቀሉ የአፍሪካ አገራት መሆን ችለዋል።