ቀጥታ፡

የመንግስትን መስሪያ ቤቶች ግብይት ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ስርዓት ለመተካት እየተሰራ ነው- የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2015 (ኢዜአ)፡- በሁለተኛው የሪፎርም ምዕራፍ የመንግስትን መስሪያ ቤቶች ግብይት ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ስርዓት ለመተካት እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ተናገሩ።

የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጋራ ፕሮጀክት የሆነው የመንግስት የግዥ ካርድ ዛሬ ይፋ ሆኗል።

የመንግስት ዲጂታል የግዥ ካርድ፤ ተቋማት ያለምንም ቼክ በዲጂታል መንገድ ግዥ ለመፈጸም የሚያስችላቸው ሲሆን የመንግስት ወጪ በአግባቡ ለመምራት ያግዛል ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በዚህ ወቅት እንዳሉት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አንዱ ቁልፍ ዘርፍ የዲጂታል ሽግግር ዕውን ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂን ዕውን ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶለት ወደስራ የተገባና መንግስታዊ የሕግ መሰረት ያለው የዲጂታል ስትራቴጂ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ነው ያነሱት።

የመንግስት ክፍያ ስርዓትን በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማስገባት አንዱና ዋነኛ ስራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ዕውን ማድረግ የክፍያ ስርዓትን ከማሻሻል ባለፈ የፋይናንስ ተጋላጭነት በመቀነስ በኩል ፋይዳው የጎላ ነው።

የጥሬ ገንዘብ ግብይት በብዙ መልኩ ተመራጭ ባለመሆኑ አጠቃላይ የዲጂታል ስርዓትን በማስፋፋት የመንግስትን ወጪና ገቢ ግብይትን በኤሌክትሮኒክ ስርዓት  ተፈጻሚ ይደረጋል ብለዋል።

በሁለተኛው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ሁሉንም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወደ ዲጂታል ግብይት አገልግሎት እንዲገቡ መታቀዱን ተናግረዋል።

እስካሁን የዲጂታል ግብይት ስርዓት ተፈጻሚ በሆነባቸው ተቋማት ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።


 

በፋይናንስ ዘርፉ በየጊዜው የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተሻለ አገልግሎት እንዲያቀርቡ፤ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም በፍጥነት ወደዲጂታል ግብይት አሰራር እንዲገቡ አሳስበዋል።

በዕለቱ ይፋ የተደረገው የመንግስት ግዥ ካርድ ለፌዴራል ተቋማት ለማሰራጨት መታተሙን ገልፀው፤ በቀጣይም በክልሎች እንደሚሰፋ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ የዲጂታል ግብይት ስርዓት ማለማመድ ለረጅም ጊዜ ፈተና ሆኖ ቢቆይም፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ በመንግስት ከመጣ በኋላ ትልቅ ለውጥና መነቃቃት አምጥቷል ብለዋል። 


 

የኤሌክትሮኒክ የግብይት ስርዓት በአጭር ጊዜ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ 3 ነጥብ 3 ትሪሊዮን በዲጂታል ግብይት በኩል ገንዘብ መንቀሳቀሱን ተናግረዋል።

ይህም የባንኩን ካፒታል ሶስት ዕጥፍ ገዳማ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዕለቱ ይፋ ከሆነው የመንግስት የግዥ ካርድ በተጨማሪ ሌሎች የክፍያ አገልግሎት ለመስጠት የሚስችሉ አሰራሮች እንደሚጀመሩ ተናግረዋል።

ባንኩ የመንግስት ተቋማት ግዥ ካርድ ሃላፊነት በተሰጠው መሰረት የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በበጀት ዓመቱ በዲጂታል አገልግሎት የተሻለ አፈፃፀም የነበራቸው ተቋማት ዕውቀትና ተሰጥቷቸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም