በመጪው የበጋ ወቅት የደቡብና የደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል -ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
በመጪው የበጋ ወቅት የደቡብና የደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል -ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2015 (ኢዜአ)፦በመጪው የበጋ ወቅት ሁለተኛው የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በ2016 ዓ.ም ከጥቅምት እስከ ጥር ወር የሚኖረውን የበጋ ወቅት የአየር ሁኔታ ትንበያ ይፋ አድርጓል።
በበጋው ወራቶች የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዝዳንት ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ይችላል።
በዚሁ ወቅት በደቡባዊ ሶማሌ፣ በደቡብ የኦሮሚያና የደቡብ የአገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉም ትንበያዎች ያመለክታሉ ነው ያሉት።
በተጨማሪም የደቡብና የደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሲኖራቸው፤ የምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛ ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛውና በምስራቁ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ከ5 ዲግሪ ሴልሽየስ በታች ሊሆን እንደሚችል ትንበያዎች ያመለክታሉ ብለዋል።
በዚህ ዓመት የድርቅ ስጋት ባይኖርም በተቃራኒው ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችልም ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የሰሜን፣ ሰሜን ምስራቅ፣ ምስራቅ እና መካከለኛ አካባቢዎች መደበኛ ዝናብ እንደሚያገኙ ነው የገለጹት።
በእነዚህ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም የበልግ ወቅት ዝናብ ፈጥኖ የመግባትና ዘግይቶ የመውጣት አዝማሚያ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።
የሚገኘው የዝናብ ስርጭት ለግብርና ስራ እና የውሃ አካላት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተገልጿል።
በዚህም ህብረተሰቡ ለግብርና እና ለሌሎች ስራዎች ያለውን ዝናብ በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት በመልዕክታቸው አስተላልፈዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለሰ መኮንን በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የሚሰጣቸውን መረጃዎች በመጠቀም ለግብርና ስራዎች እንዲውሉ ይደረጋል ነው ያሉት።
በዚህም ኢንስቲትዩቱ የሚሰጣቸውን የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎችን በመጠቀም የበለጠ ምርታማነት ለማጠናከር እንደሚሰራም አብራርተዋል።