ቀጥታ፡

የጳጉሜን ቀናት የኢትዮጵያ የአብሮነትና ሕብረ ብሔራዊ እሴቶችን በሚያጸኑ ክንውኖች የሚከበሩ ይሆናል - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2015 (ኢዜአ)፡- ስድስቱ የጳጉሜን ቀናት የኢትዮጵያ የአብሮነትና ሕብረ ብሔራዊ እሴቶችን በሚያጸኑ ክንውኖች የሚከበሩ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ። 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በ2015 ዓ.ም የተመዘገቡ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እንዲሁም ስድስቱን የጷግሜን ቀናት አከባበር አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ፤ ስድስቱ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብረው እንደሚውሉ ገልጸዋል።

ስድስቱ ቀናት የአብሮነት እሴትን በሚያሳድጉ፣ የአገልጋይነት ባህልን በሚያጎለብቱና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጸኑ ዝግጅቶች እንደሚከበሩ ተናግረዋል።  

የስድስቱንም የጳጉሜን ቀናት ዝግጅቶች የሚመሩና የሚያስተባብሩ የፌደራልና የክልል ተቋማት በተዋረድ እንደተሰየሙም ተናግረዋል።

የጳጉሜን 1 ቀን "የአገልግሎት ቀን" ሆኖ በመንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገርና ህዝብን ማገልገል የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ የሚፈጠርበት ይሆናል ብለዋል።

የጳጉሜን 2 "የመስዋትነት ቀን" የተሰየመ ሲሆን በዕለቱ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ሚሊሻና ፖሊስ የሚዘከሩበት መሆኑን ገልጸዋል።

በጸጥታ ተቋማት የማገልገል ጥቅም የተመለከቱ ጉዳዮችና ወጣቶችም የጸጥታ ተቋማትን ተቀላቅለው አገራቸውን እንዲያገልግሉ ጥሪ የሚደረግበት ዝግጅት እንደሚኖርም ተናግረዋል።

በጳጉሜን 3 "የበጎነት ቀን" በሚል ተሰይሞ ኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ ታሪክና ውጤት የሚዘከርበት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጥቅምና ምንነት ግንዛቤ ይሰጣል ብለዋል።

ጳጉሜን 4 ደግሞ "የአምራችነት ቀን" በሚል ገንዘብና ሃብታቸውን በአገራቸው አውለው በግብርና፣ በኢንዱስትሪና ሌሎች መስኮች አገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ የሚገኙ ዜጎች ይዘከራሉ ብለዋል።

የአገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህልን ማጎልበት የሚኖረው ጠቀሜታም ግንዛቤ እንደሚፈጠር ተናግረዋል።

ጳጉሜን 5 "የትውልድ ቀን" በሚል ስያሜ የአሁኑ ትውልድ የተረከባትን አገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ዝግጅት እንደሚደረግ አመላክተዋል።

የመጨረሻዋ ጳጉሜን 6 ደግሞ "የአብሮነት ቀን" በሚል ስያሜ በተለያዩ ብዝሃነትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጸኑ ዝግጅቶች ተዘክሮ እንደሚውል ገልጸዋል።

በዕለቱም ቤተሰብን፣ ሕዝብና አገርን ስለመውደድ፣ በሰላምና ፍቅር ስለመኖር የተመለከቱ ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም