በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ለጤና ጠንቅ የሆኑ ከ13ሺህ ቶን በላይ ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶች ተወግደዋል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ለጤና ጠንቅ የሆኑ ከ13ሺህ ቶን በላይ ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶች ተወግደዋል
አዳማ ፤ ነሐሴ 25/2015(ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ለጤና ጠንቅ የሆኑ ከ13ሺህ ቶን በላይ ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን ማስወገዱን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ገለፀ።
ባለስልጣኑ በ2015 በጀመት ዓመት በምግብና መድሃኒት ላይ ከቁጥጥርና ጥራት አንፃር ያለውን ዕቅድ ክንውንና የአዲሱ በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ ጥራትና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ ምግቦችና መድሃኒቶች ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ተደራሽ እንዲሆን ሰፊ የቁጥጥር ስራ ተሰርቷል።
ከእነዚህም በትምባሆ፣ ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ቁጥጥር እንዲሁም መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ደህንነትና ፈዋሽነት ላይ በተሰሩ ስራዎች ውጤት መመዝገባቸውን ለአብነት አንስተዋል።
በተለይም ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ባዕድ ነገሮችን መቀላቀል፣ የአገልግሎት ጊዜያቸውና የተመረቱበት ሀገር የማይታወቁ የመድኃኒትና ምግብ ምርቶች ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ባለስልጣኑ የልህቀት ማዕከል ግንባታ ከማስጀመር ባለፈ የኤች አይ ቪ፣ የወባ ክትባት ላቦራቶሪ እንዲሁም የምግብና ሌሎች ተያያዥ ላቦራቶሪዎች የማደራጀት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠውን የቁጥጥርና ጥራት ደረጃ 3 ላይ ለመድረስ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተሰራው ስራ የመድኃኒት ፈዋሽነት ላቦራቶሪ ISO 17020 ማስቀጠል መቻሉን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ በምግብ ደህንነት ፍተሻ ላቦራቶሪ ISO 17025 ዕውቅና ማግኘቱን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም በግብዓት የማደራጀት ስራ መሰራቱንም አመልክተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መንግሥቱ በቀለ በበኩላቸው በክልሉ በምግብ ምርቶች ደህንነትና በህክምና መሳሪያዎችና መድሃኒቶች ፈዋሽነት ቁጥጥር ላይ ከባለስልጣኑ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ክልሉ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ዓለም አቀፍ ድንበሮች የሚጋራ በመሆኑ ህገ ወጥ የምግብና መድሃኒት ንግዶችና ኮንትሮባንድ መድኃኒቶች፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ከመቆጣጠር አንፃር ባለስልጣኑ እያገዘን አብረን እየሰራን ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው የምግብ ምርቶች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡና ደህንነታቸው ያልተረጋገጡ የምግብ ምርቶች በገበያ ላይ እንዳይውሉ ቁጥጥርና የጥራት ደረጃቸውን የመከታተል ስራ መሰራቱን የገለጹት ደግሞ በባለስልጣኑ የዕቅድ ዝግጅትና ግምገማ ኬዝ ቲም አስተባባሪ ወይዘሮ ፋኢዛ ቢያ ናቸው።
በተለይም የምግብና መድኃኒት አምራች ድርጅቶች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮች በመውጫና መግቢያ ኬላዎች ላይ የተሻለ የቁጥጥር ስራ መሰራቱን ገልአንስተዋል።
በዚህም 13ሺህ 319 ቶን የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የምግብ ምርቶችና ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተመረቱበት ሀገር የማይታወቅና የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቃ የህክምና መድኃኒቶች መወገዳቸውን አስተባባሪዋ ተናግረዋል።
በተጨማሪም 76 ምግብ አምራች ተቋማት ላይ የማምረት ዕግድ ከመጣሉም ባለፈ 14 የምግብ ምርቶች አስመጪና አካፋፋዮች ላይ የማሸግ እርምጃ መወሰዱንም አክለዋል።
በተመሳሳይ 700 የሚሆኑ አስመጪና አከፋፋዮች በአግባቡ ፍቃዳቸውን ባለማሳደሳቸው ፍቃዳቸውን የመሰረዝ እርምጃ መወሰዱንም ጨምረው ገልጸዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ የምግብና መድሃኒት ምርቶች ላይ በቁጥጥርና ደህንነት በማረጋገጥ ስራዎች ረገድ የተሻለ አፈፃፀም የተመዘገበበት መሆኑንም ተናግረዋል።