ቀጥታ፡

“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ እውን እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ዶክተር በለጠ ሞላ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2015 (ኢዜአ)፦ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን እውን  ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ገለጹ። 

“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ በዋናነት የዲጂታል መሰረተ ልማት በመገንባትና በማስፋት የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ ነው።  

ስትራቴጂው ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ የተቀረጸ ነው። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የስትራቴጂውን ያለፉት ሦስት ዓመታት የመካከለኛ ዘመን አፈጻጸም እየገመገመ ነው።  


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በዚሁ ጊዜ ስትራቴጂው በኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን አሰራር ትርጉም ባለው መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ ስትራቴጂው ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ነው የተናገሩት። 

በተለይም የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በመዘርጋት፣ የዲጂታል አገልግሎት በማስፋት እንዲሁም የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ በማድረግ አመርቂ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። 

እነዚህም ተግባራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።  

ያም ሆኖ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውን ከማድረግ አንጻር አሁንም የሚቀሩ በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸው የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት። 

ዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን እውን ለማድረግ የቴሌኮም፣ የመብራትና መሰል መሰረተ ልማቶች ወሳኝ መሆናቸውን አንስተው ተደራሽነታቸውን ለማስፋት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።  

በቀሪዎቹ ሁለት ዓመታት “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025”ን  እውን ለማድረግ በተለይ ባለድርሻ አካላት እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። 

የግምገማ መድረኩ እስከ ነገ የሚቀጥል ሲሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት ተገምግመው የቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡ ይሆናል ተብሏል። 

 
 
  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም