ቀጥታ፡

በ2016 የትምህርት ዘመን አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በሁሉም የኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ይደረጋል- የትምህርት ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2015(ኢዜአ)፦ በ2016 የትምህርት ዘመን አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።  

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በትምህርት ዘርፉ ላይ የተደረገውን ለውጥና የተከናወኑ ሥራዎችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በአጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የነበረውን ስብራት ለመጠገን መሰረት የሚጥሉ የለውጥ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል።

በ2016 የትምህርት ዘመን አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

የመጻሕፍት ሕትመትና ስርጭት ችግሮችን ለመፍታትም ከውጭ አታሚዎች ጋር ጭምር በመዋዋል እስከ መስከረም ወር ድረስ ለትምህር ቤቶች ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። 

  የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዙ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሩም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሟላት ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኅብረተሰቡን በማስተባበር ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉንም ገልጸዋል። 

በተጨማሪም በ2016 የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች የሚስተናገዱባቸው አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በተለያዩ ክልሎች ይጀመራል ብለዋል። 

የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹን ግንባታም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ በ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደሚጀመር ገልፀዋል።

ጎን ለጎንም በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የኢንተርኔት አገልግሎት ባለባቸው አካባቢዎች በኦንላይን /በቀጥታ/ እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም