የኢትዮጵያን እድገት ዘላቂ ለማድረግ የጥናትና ምርምር ተቋማት የላቀ ሚና ማበርከት ይጠበቅባቸዋል-ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን እድገት ዘላቂ ለማድረግ የጥናትና ምርምር ተቋማት የላቀ ሚና ማበርከት ይጠበቅባቸዋል-ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2015(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የልማት እቅድ እውን በማድረግ ዘላቂ እድገት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የጥናትና ምርምር ተቋማት የላቀ ሚና የሚጠበቅባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የጥናትና ምርምር ተቋማት ፎረም ዋና ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ገለጹ።
የፌዴራል የጥናትና ምርምር ተቋማት ፎረም በዛሬው እለት በይፋ ተመስርቷል።
ፎረሙ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲቲዩት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ፣የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትና ሌሎች የጥናትና ምርምር ተቋማትን ያካተተ ነው።
በፎረሙ የተካቱት አስራ ሶስት ተቋማት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድም ተፈራርመዋል።
የፎረሙ ምስረታ ዋና ዓላማ በቀጣይ ኢትዮጵያ ለምታካሄዳቸው የልማት እቅዶች በጥናትና ምርምር የተደገፉ የፖሊሲ አማራጮችን ለማቅረብ መሆኑ ተገልጿል።
በምርምር ተቋማት መካከል ትብብር በማስፈን እውቀት መጋራትን ማመቻቸትና የምርምር ውጤቶችን ለማስፋት እንደሚያግዝም ተመላክቷል።
የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የጥናትና ምርምር ተቋማት ፎረም ዋና ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ የምርምር ተቋማት ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት አበርክቶው ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የልማት እቅድ እውን በማድረግ ዘላቂ እድገት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የጥናትና ምርምር ተቋማት የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የፎረሙ መመስረትም ለኢትዮጵያ የልማትና እድገት እቅድ ስኬት ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተርና የፎረሙ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ደሳለኝ አምበው፤ የፎረሙ ምስረታ የምርምር ተቋማት አቅማቸውን በማጎልበት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የምርምር ተቋማቱ በሀገረ መንግስት ግንባታና የልማት አቅዶቸን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ተሳትፏቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ከፎረሙ አባላት መካከል የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ፤ የምርምር ተቋማት አንድ ላይ በመሆን ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶች ለይ በትኩረት እንዲሰሩ የፎረሙ መመስረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የግብርና ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂዮ ስፓሻል ኢንስቲትዩት፣ የባዮና ኢመርጀንሲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት፣ አርማወርሃንሰን የጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የህብረተሰብ ጤና አገልግሎት፣ የፌዴራል የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ዳያስፓራ አገልግሎት በፎረሙ ተካተዋል።