የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ ለካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ማለፍ አልቻለም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ ለካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ማለፍ አልቻለም

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 24/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ ባደረገው የፍጻሜ ጨዋታ በታንዛንያው ጄኪቴ ኩዊንስ በመለያ ምት ተሸንፏል።
በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከነሐሴ 6/2015 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።
በ ‘FUFA Technical Center Stadium’ በተካሄደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የታንዛንያው ጄኪቴ ኩዊንስ ጨዋታ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜና በጭማሬ 30 ደቂቃ ግብ አልተቆጠረም።
አሸናፊውን ለመለየት ጨዋታው ወደ መለያ ምት ያመራ ሲሆን ጄኪቴ ኩዊንስ 5 ለ 4 በማሸነፍ የሴካፋ ዞንን ወክሎ በኮትዲቭዋር አቢጃን በሕዳር ወር 2016 በሚካሄደው ሶስተኛው የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉን አረጋግጧል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን አጠናቋል።
በዩጋንዳ ካምፓላ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በስታዲየሙ በመገኘት ለቡድኑ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ከፍጻሜ ጨዋታ በፊት በተደረገው የደረጃ ጨዋታ የብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ የኬንያውን ቪሂጋ ኩዊንስን 1 ለ 0 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ከዚህ ቀደም በኬንያና ታንዛንያ በተካሄዱ የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድሮች በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።