ቀጥታ፡

አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2015(ኢዜአ)፦የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ክሪስ ኒኮይ ጋር ተወያይተዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ ሚኒስትር ዴኤታው በውይይቱ ላይ አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው የዓለም ምግብ ፕሮግራምና መሰል ተቋማትም ይሄንኑ ለማጠናከር የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን ከአድሎዓዊ አሠራር በፀዳ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ መንግስት ከሁሉም ግብረ-ሠናይ አካላት ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ክሪስ ኒኮይ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ለተጎዱ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማገዝና በትብብር ለመስራት መስማማታቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም