ቀጥታ፡

የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ለሀገራዊ እድገት ያላቸውን አስተዋጾ ማጎልበት የሁሉም ኃላፊነት ነው--የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን

ድሬደዋ፣  ነሐሴ 24/2015 (ኢዜአ) የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለሀገራዊ እድገት ያላቸውን አስተዋጾ ማጎልበት የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

በድሬዳዋ አስተዳደር ለተመዘገቡ 56 ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ቅርሶች ባለቤቶችና ባለይዞታዎች ዛሬ የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

በእዚህም የቅርስነት የዕውቅና ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው የተለያዩ ቅርሶች፣ ተቋማትና ባለቤቶች መሆናቸው ተመሏክቷል።

የድሬደዋ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ከፌደራል የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት ላጠናቸው ሰው ሰራሽ ቅርሶች እና በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ሰው ይኖርባቸው ለነበሩ የተፈጥሮ የዋሻ ቅርሶች ዛሬ የእውቅና ማረጋገጫ ተሰጥቷል።

ከዕውቅናው በተጨማሪ በድሬደዋ ከተማ የሚገኘውን "የእንቁፍቱ" የተፈጥሮ ዋሻን ለቱሪስት መዳረሻ ምቹና ሳቢ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ጉብኝት ተደርጓል።


 

በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሐይሉ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ያሉ የማንነት መገለጫ የሆኑ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች ተጠብቀው ለአገር ልማትና ዕድገት አስተዋጾ እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው።

ቅርሶቹን ጠብቆና ተንከባክቦ በማቆየት ለሀገር እድገት ያላቸውን ጠቀሜታ የማጎልበት ሥራም ለአንድ ተቋም የሚተው ሳይሆን የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት መሆኑን አስታውቀዋል።

ድሬዳዋ በርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች እንዳሏት ጠቅሰው፣ ከነዚህ ቅርሶች መካከል ለ56ቱ ዕውቅና መሰጠቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም የዕውቅና መስጠቱ ሂደት እንደሚጠናከር የጠቆሙት ወይዘሮ ህይወት፣ ባለስልጣኑ በድሬዳዋ በሚገኘው የእንቁፍቱ ዋሻ ካካሄደው የጥገና ስራ በተጨማሪ ለከተማዋ መቆርቆር መሠረት ለሆነው የምድር ባቡር ተርሚናል በ4 ሚሊዮን ብር ጥገና ለማድረግ የጥናት ሥራው መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በድሬደዋ የሚገኙ ተቋማት ቅርሶችን ከነሙሉ ይዞታቸው ጠብቀው ለትውልድ ለማስተላለፍ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ያስመሰግናል" ያሉት ምክትል ዳይሬክተሯ፣ በቀጣይም ቅርሶች ለአገር ከፍታ እና ለቱሪስት መዳራሻ እንዲሆኑ ሁሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበዋል።


 

የዕውቅና የምስክር ወረቀቱን ለተቋማት ተወካዮች የሰጡት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፣ በአስተዳደሩ የሚገኙ ቅርሶችን ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በድሬደዋ ከተጠኑት ከ80 በላይ ቅርሶች መካከል ዛሬ ለ56ቱ የተሰጠው ዕውቅና ቅርሶች ለአገር እድገት ያላቸውን ፋይዳ ለማሳደግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ቅርሶችን ለድሬዳዋ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት ዕድገት ለማዋል የሚከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ነዋሪዎች ቅርሶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነታቸውን ከምንግዜውም በላይ እንዲወጡ ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ታሪካዊ ቅርሶችንና የጋራ ባህላዊ እሴቶችን የመመዝገብ፣ የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ መሰራቱን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ የባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ ናቸው።


 

ቅርሶቹ ለማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብት ዕድገት እንዲውሉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት እነዚህ ስራዎች ቢከወኑም የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የበለጠ ተግቶ መስራት ያስፈልጋል።

በዛሬ ዕለት ዕውቅና የተሰጣቸው የትምህርት፣ የሃይማኖት ተቋማትና የተለያዩ ድርጅቶች ተወካዮች በሰጡት አስተያየት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶችን ይበልጥ በመጠበቅ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ይበልጥ ተግተው ለመስራት መዘጋጀታቸውን አረጋግጥዋል።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም