ቀጥታ፡

የውሃና ኢነርጂ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ኢትዮጵያ ለሳይንስና ምርምር የሰጠችውን ትኩረት የሚያመላክቱ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2015(ኢዜአ)፦የውሃና ኢነርጂ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ኢትዮጵያ ለሳይንስና ምርምር የሰጠችውን ትኩረት የሚያመላክቱ መሆናቸውን የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና የመከላከያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ድርጅት ሰራተኞች ገለጹ፡፡

የሰራዊቱ አባላትና የድርጅቱ ሰራተኞች በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የውሃና ኢነርጂ አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል። 

በአውደ ርዕዩ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ እንደ አገር የተከናወኑ ስራዎች በተለይም በውሃ ቴክኖሎጂና ኃይል ልማት ዘርፍ የተገኙ ስኬቶች ለእይታ ቀርበዋል።

የመከላከያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ድርጅት የሰርቬየር ቡድን መሪ ሻለቃ ደበበ እሸቱ፤ በአውደ ርዕዩ የቀረቡ ስራዎች በኢትዮጵያ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ዘርፍ እያከናወነች ያለቸውን ተግባራት የሚያሳዩ ናቸው። 


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ አገልግሎታቸውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ከማድረግ አንጻር ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን የሚያመላክት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ በሳይንስ ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረች ለመሆኑ ማሳያ ነው ያሉት ሻለቃ ደበበ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተቋማቸው በመውሰድ የላቀ ስራ ለማከናወን መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

የመከላከያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ድርጅት የሳኒተሪ ቡድን መሪ ኢንጂነር ትዕግስት መቻል በበኩላቸው፤ ከአውድ ርዕዩ ለተቋማቸው የሚሆን በርካታ ግብዓቶችን ማግኘታቸውንና ተሞክሮዎችን በመውሰድ በቀጣይ የተሻሉ ስራዎች እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም አዱኛ በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች አውደ ርዕዩን  መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና የመከላከያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ድርጅት ሰራተኞች በጉብኝታቸው የተሻለ ልምድ በመውሰድ ተግባራዊ አንደሚያደርጉም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።  

የውሃና ኢነርጂ አውደ ርዕይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼኽ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም መከፈቱ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም