ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ  በ2016  የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ተጀመረ

ጎንደር ፤ ነሐሴ 24/ 2015 (ኢዜአ) ፡- በጎንደር ከተማ በ2016 የትምህርት ዘመን ከ94 ሺህ በላይ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መጀመሩን  የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የትምህርት ዘመኑን የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ለማስጀመር የሚያስችል የአንድ ጀምበር የተማሪዎች ምዝገባ መርሃ ግብር ዛሬ በከተማው መሰረት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተካሂዷል፡፡


 

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ዳንኤል ውበት በወቅቱ እንዳሉት፤በከተማው የሰፈነው ሰላም ለትምህርት ስራ ንቅናቄ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

በትምህርት ዘመኑ በአንደኛ ደረጃ 66 ሺህ 456 እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ 27ሺ 583 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር  በከተማው በሚገኙ 84 ትምህርት ቤቶች ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የመማር ማስተማር ስራውን ስኬታማ ለማድረግም ትምህርት ቤቶችን በግብአት በማሟላት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

የከተማውን ትምህርት ቤቶች ደረጃ በማማሻሻልም በ89 ሚሊዮን ብር ወጪ ባለፈው ዓመት ግንባታቸው ከተጀመሩ 29 የመማሪያ ክፍሎች መካከል ለዘንድሮ ዓመት 16 የመማሪያ ክፍሎች ስራ ይጀምራሉ ብለዋል፡፡

በከተማው የሰፈነው ሰላም ዛሬ  ለተጀመረው የአንድ ጀንበር የተማሪዎች ምዝገባ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል  ያሉት የመሰረት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ስጦታው አምሃ ናቸው፡፡ 

በትምህርት ዘመኑ ትምህርት ቤቱ 1ሺህ 887 ተማሪዎችን በአንድ ቀን መዝግቦ ትምህርት ለማስጀመር ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን እያስመዘገቡ ይገኛል ብለዋል።


 

የተማሪ ወላጅ ወይዘሮ እመቤት ጫኔ በሰጡት አስተያየት፤ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ልጃቸው የመማር ማስተማር ስራውን በወቅቱ እንድትጀምር ምዝገባ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።

በከተማው በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ ከክፍያ ነጻ መደረጉ የመክፈል አቅም ለሌላቸው ወላጆች እፎይታ የሰጠ መሆኑን የገለጹት አቶ አበራ ጌታሁን ናቸው። 

የአምስተኛ ክፍል ተማሪዋ ሰሎሜ ጋሻው በበኩሏ፤ በከተማው የሰፈነው ሰላም እኛ ተማሪዎች የነገ ህልምና ተስፋችን እንዲቀጥል ያደረገ በመሆኑ ትምህርት ለመጀመር ተመዝግቤያለሁ ብላለች፡፡

በጎንደር ከተማ ዛሬ የተጀመረው የተማሪዎች ምዝገባ እስከ ጷጉሜን  5 የሚካሄድ ሲሆን መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራው በይፋ እንደሚጀመር በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም