በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ የአደጋ ስጋቶችን ቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክት ሊተገበር መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ የአደጋ ስጋቶችን ቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክት ሊተገበር መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 24/2015 (ኢዜአ) ፡- በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ የአደጋ ስጋቶችን ቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ “ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለሁሉም” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ።
ፕሮጀክቱ በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ዋና አስተባባሪነት እንደሚተገበርም ተጠቁማል።
የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ አውደ ጥናት የተመለከተ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል።
በአውደ ጥናቱ ላይ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረግባቸው አገራት ተወካዮችና አጋር አካላት ተገኝተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም አዱኛ፤ "ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለሁሉም" ፕሮጀክት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሰው ልጆችን ከአስጊ የአየር ሁኔታ፣ ከአየር ንብረት ክስተቶችና ከውሃ ዑደት ለውጥ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ችግሮች እንዲጠበቅ የሚያደርግ ፕሮጀክት ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ ከውሃና አየር ንብረት ለውጥ ክስተቶች ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመቀነስና የተጎጂውን ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም አቅም ለማሳደግ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አማካኝነት ለሚተገበረው ፕሮጀክት 30 አገራት መመረጣቸውንና ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ዩጋንዳ በፕሮጀክቱ ትግበራ የተካተቱ የአፍሪካ አገራት መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያ በዚህ ፕሮጀክት ተመራጭ እንድትሆን ያደረጋት አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረገች ያለችው አስተዋጽኦ እና ከቅድመ ማስጠንቀቂያ ጋር በተያያዘ ያላት ዘርፈ ብዙ የአየር ንብረት አገልግሎት መሆኑንም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ ከ2023 እስከ 2028 ለአምስት አመታት እንደሚቆይም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተፈጠሩ በርካታ ችግሮች በዜጎች ላይ ተፅእኖ ማሳደራቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አደጋዎችን ከመከላከል አኳያ የአደጋ ስጋት አመራርና የአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ብለዋል።
በመሆኑም ፕሮጀክቱ አደጋ ከመከሰቱ በፊት የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ በመስጠት ሊደርስ የሚችልን አደጋ መከላከል ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ፀሐፊ ጌታቸው ታአ፤ የቅደመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ የአደጋ ተጋላጭነትን በእጅጉ ይቀንሳል ብለዋል።
ለዜጎች አደጋን አስመልክቶ ከሚሰጥ መረጃ ባለፈ አደጋ ሲያጋጥም መቋቋም የሚችሉበትን አቅም መፍጠር ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አክለዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና በዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ትብብር የተዘጋጀው አውደ ጥናት ከዛሬ ጀምሮ ለሶሰት ቀናት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።