ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የባለድርሻ ተቋማት ትብብር ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል- የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24 / 2015 (ኢዜአ) ፡- በኢትዮጵያ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ባለድርሻ ተቋማት ያላቸውን ትብብር ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።   

የኢትዮጵያ የእንስሳት ሐኪሞች ማኅበር 36ኛው ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል።     

ጉባዔው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፤ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ባለድርሻ አካላት፣ የልማት አጋሮችና የሙያ ማኅበራት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡   

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ኃብት ልክ  እንዳትጠቀም ከሚያደርጓት ጉዳዮች መካከል አንደኛው የእንስሳት ጤና ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡          


 

የእንስሳት ጤና ችግር  የወጪ ንግድ ገቢ ላይ አሉታዊ ጫና የማሳደር አቅም እንዳለውም ነው የጠቆሙት፡፡       

የእንስሳት ጤና በአግባቡ ካልተጠበቀ፣ የእብድ ውሻ በሽታ እና ኮሶ የመሳሰሉ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው እንደሚተላለፉም እንዲሁ፡፡       

የእንስሳት ጤና በማስጠበቅ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ጥቅም እንድታገኝ ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም በተለያዩ ክልሎች የእንስሳት ጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ከማስፋፋት ጎን ለጎን አስፈላጊ የሕክምና ቁሳቁሶች እንዲያሟሉ እየተደረገ  መሆኑን ተናግረዋል።     

በሽታዎችን ለመከላከል በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የክትባት አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን መደረጉን  ጠቅሰው፤ ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከል 200 ሺህ ውሾች በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከተቡ ተደርጓል ብለዋል።     

በተጨማሪም የ"ደስታ" በሽታን በአሥር ዓመት ውስጥ ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡      

የእንስሳት ጤና እና ደኅንነት አዋጅ ሥራ ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ መጀመሩ እየተሰሩ ካሉ ሥራዎች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።    

ኢትዮጵያ ከእንስሳት ኃብት ተጠቃሚ በማድረግ ሂደት የእንስሳት ጤና ባለሙያዎችም ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ረገድ ባለሙያዎች ምክረ-ሀሳብ በማቅረብ፣ ከመንግሥት ጋር ተናቦ በመሥራት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።   

የኢትዮጵያ የእንስሳት ጤና ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ቦጃ እንደቦ በበኩላቸው፤ ማኅበሩ በዓመት ሁለት ጊዜ በጀት በመመደብ ጥናቶችን በማድረግ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል።     

በአሁኑ ወቅት የእንስሳት ጤና አገልግሎት እየተሰጠ ያለው በአብዛኛው በመንግሥት መሆኑን ጠቅሰው፤  በመንግሥትና የግል አጋርነት አሠራር አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ጥናቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።   

ከሚሰጠው የእንስሳት ጤና አገልግሎት ውስጥ ምን ያህሉ በመንግሥት እና በግል ጤና ተቋማት ሊሸፈኑ ይገባል? እንዲሁም የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች የክህሎት ደረጃ ምን ሊሆን ይገባል? የሚሉ ጥያቄዎች በጥናቱ እንደሚዳሰሱም አስረድተዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም