በተያዘው በጀት ዓመት በዞኑ ለ91 ሺህ በላይ ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጠራል - ምዕራብ አርሲ ዞን - ኢዜአ አማርኛ
በተያዘው በጀት ዓመት በዞኑ ለ91 ሺህ በላይ ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጠራል - ምዕራብ አርሲ ዞን
ሻሸመኔ፣ ነሐሴ 24/2015 (ኢዜአ) በ2016 በጀት ዓመት በተለያዩ ዘርፎች ከ11ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞችን በመመስረት ከ91 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የምዕራብ አርሲ ዞን የሥራ እድል ፈጠራና ክህሎት ፅህፈት ቤት ገለፀ።
የምዕራብ አርሲ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዶ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለፁት፣ የስራ ዕድል ለመፍጠር ከታቀደው ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ነው።
የስራ ዕድል ከሚፈጠርባቸው ዘርፎች መካከል ደግሞ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ማዕድን ልማት፣ የገጠር ግብርና፣ የእንስሳት ሃብት ልማት፣ አገልግሎትና ንግድ ዋነኞቹ መሆናቸውን አንስተዋል።
በተጨማሪም በግል ኢንቨስትመንትና በመንግስት ተቋማትም በቋሚና በጊዜያዊነት የስራ እድሉ የሚፈጠር እንደሚሆን ተናግረዋል።
በዚህም በዞኑ 11 ሺህ 193 ኢንተርፕራይዞችን በመመስረት 91ሺህ 832 ለሚሆኑ ስራ ፈላጊዎችን በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ነው አቶ አብዶ ያስረዱት።
ለዚህም በየአካባቢው ያሉ የስራ ዕድል መፍጠሪያ ፀጋዎችን መለየት፣ ከስራ ባህል ጋር በተያያዘም የወጣቶችን፣ የወላጆችንና የማህበረሰቡን አመለካከት ሊቀየር የሚችል ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች አስቀድመው ሲሰሩ መቆየታቸውን ሃላፊው ገልጸዋል።
የስራ ማስጀመሪያና ቴክኒካል ስልጠናዎችንም ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ጋር በመቀናጀት የማመቻቸት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።
በተጨማሪም ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ተግዳሮት ሊሆን የሚችል የብድር አገልግሎት ከሲንቄ ባንክ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
እንዲሁም የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥማቸው ጽህፈት ቤቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የስራ ማስጀመሪያ ቦታ አቅርቦት እንዲያገኙ ከአሁኑ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
"ይህን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ ማቀድ ብቻ ግብ አይደለም" ያሉት ኃላፊው፤ ሁሉም ወረዳዎች የስራ ዕድል መፍጠር ቁልፍ ስራ አድርገው እንዲንቀሳቀሱ በወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎች የሚመራው የስራ ዕድል ፈጠራ ግብረ ኃይል በመኖሩ ለተግባሩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 4 ሺህ እንተርፕራይዞችን በማቋቋም ለ83ሺህ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን ከዞኑ ሥራ እድል ፈጠራና ክህሎት ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።